AMN- ሰኔ 13/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ የመብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን አራት የሪጅን ጽ/ቤቶችን ስራ አስጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተፈራ ሞላ (ዶ/ር)፤ በከተማዋ በኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ በኩል የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንዲያስችል በቅርቡ ባለስልጣኑ መቋቋሙን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙ ከተመሰረተ ወዲህ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ስራ የጀመሩት የመጀመሪያዎቹ ሪጅኖች ደንበኞች ወደ አገልግሎት ማዕከላት ከሚመጡ ይልቅ አገልግሎቱ ወደ ደንበኞች የሚቀርብበትን ስርዓት የሚዘረጋ ነውም ብለዋል፡፡
ይሄም አገልግሎቶች ምቹና ቀልጣፋ እንዲሆኑ ያስችላልም ነው ያሉት፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰብስብ ሁሴን በበኩላቸው፤ ባለስልጣኑ ለደንበኞች ምቹ አገልግሎት የሚሰጥበትን ሁኔታ እየፈጠረ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
ጨለማ የነበሩ የከተማዋ መንገዶችን መብራ በማብራት ሕይወት ያላት ከተማን መፍጠር እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
በከተማዋ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ምቹና ደህንነታቸው የተረጋገጠ ሊሆን ይገባል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ባሁኑ ወቅት ባለስልጣኑ የተረከባቸውን 37 ሺህ የመንገድ ዳር መብራቶች በዘረጋው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ከአንድ ማዕከል እያስተዳደረ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
በታምሩ ደምሴ