ድምፅ መስጠት መብት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሐገራዊ ኃላፊነት ነው – የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

AMN – ግንቦት 23/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ልትመርጥ ሰዓታት ብቻ ቀርተዋታል።

የምርጫ ካርድ የወሰዱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ድምጻቸውን ለመስጠት የነገውን ዕለት በከፍተኛ ጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ለኤ ኤም ኤን በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡ መራጮች እንደገለጹት ፣ ድምፅ መስጠት መብት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነትም ጭምር ነው።

አቶ አትክልት ደስታ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውንና መብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ሲገልጹ ፣ አቶ በትዕግስት ፅጌ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ሊመራ ይገባል ብለው ለመረጡት ፓርቲ ድምጽ ለመስጠት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

ወ/ሮ ቀነኒ ሙለታ እርሳቸውን ጨምሮ አራት የቤተሰባቸው አባላት ካርድ ወስደው ድምጽ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡ መራጮች የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ቅስቀሳና የሚዲያ ክርክሮች በንቃት ሲከታተሉ እንደነበርና የትኛውን ፓርቲ መምረጥ እንዳለባቸው ለመወሰን የሚረዳ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

አቶ አንድነት ጌሻ ዜጎች ድምጻቸውን የሚሰጡት ለሀገር እድገትና የወደፊት ትልምን የሚወስን መሆኑን በመረዳት ሊመርጡ ይገባል ብለዋል።

በተመሳሳይ አቶ ፍቃዱ መርጋ ዕድሜው የደረሰ ማንኛውም ዜጋ ለወደፊት ለሐገር ይጠቅማል የሚሉትን መሪ መምረጥ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው ፣ እያንዳንዱ ዜጋ በከፍተኛ ዲሲፕሊን ድምፅ መስጠት እንዳለበት መልዕክት አስተላልፈዋል።

ለኤ.ኤም.ኤን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሁሉም መራጭ በትዕግስትና በተረጋጋ መንፈስ ምርጫውን ማካሄድ እንዳለበትም ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review