AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካሂዷል፡፡
ባለስልጣኑ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ጋር በጋራ በመሆን ባካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ላይ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የደንብ ኦፊሰሮች እና በየደረጃው ያሉ የሥራ ሃላፊዎች ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ፤ በዘንድሮው ክረምት ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ የደም ልገሳና የአቅመ ደካሞችን ቤት መገንባት ጨምሮ ልዩ ልዩ በጎ ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
ባለስልጣኑ ራሱን በማዘመንና ተልዕኮውን በላቀ የቴክኖሎጂ እገዛ በትጋት እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አህመድ ሀሰን በበኩላቸው፤ በ2018/19 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተስፋችንን በመትከል የከተማዋን ራዕይ የምናሳካበት ነው ብለዋል።
የተከልናቸውን ችግኞች የመንከባከብና የማጽደቅ ኃላፊነት አለብን ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የደንብ አስከባሪዎች በበኩላቸው፤ የተከልናቸውን ችግኞች በየጊዜው እየተንከባከብን እንዲጸድቁ እናደርጋለን ብለዋል።
በምትኩ ተሾመ