AMN – ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታሪክን ከዘመናዊ የከተማ ፕላን ጋር በማቀናጀት የጀመረው የወንዞች ዳርቻ ልማት፣ የነዋሪዎችን ማህበራዊ ኑሮና የአካባቢውን ስነ-ልቦና ሙሉ በሙሉ እየቀየረው ይገኛል።

ከሰሜን አዲስ አበባ ተነስቶ ከተማዋን ሰንጥቆ የሚፈሰው የቀበና ወንዝ፣ በታሪክ መዛግብት በ1902 ዓ.ም የመጀመሪያው የመንገድ ድልድይ የተገነባበት ቀዳሚ ስፍራ ቢሆንም፣ ለበርካታ ዓመታት ግን በክረምት ወቅት የነዋሪዎች ስጋት ሆኖ ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅት በተተገበረው አጠቃላይ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ግንባታ፣ ይህ ቀደም ሲል የጎርፍ አደጋ ቀጣና የነበረው ስፍራ፣ አሁን ላይ ደኅንነቱ የተጠበቀና ማራኪ የሕዝብ መዝናኛ ሆኗል።

በወንዙ ዳርቻ የተገነቡት ዘመናዊ መከላከያ ግንቦች የአካባቢውን ስጋት ሙሉ በሙሉ ያስቀሩ ሲሆን፣ የተተከሉ ጥቅጥቅ ያሉ ዛፎችና የተዘረጉት አረንጓዴ ስፍራዎችም የአካባቢውን አየር ንብረት በመፈወስ ረገድ ከፍተኛ ሚና እያበረከቱ ነው።
ከከተማ ውበት ባለፈ፣ ፕሮጀክቱ ያካተታቸው ሰፊ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ ክፍት የኪነ-ጥበብ መድረኮችና የንግድ ማዕከላት ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለወጣቶች አዳዲስ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ እየሆኑ ይገኛሉ።
ይህ የቀበና ፕሮጀክት እንደ ደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል ከተማ የቼኦንግዬቼኦን ወንዝ ልማት የከተማዋን ሙቀት ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
በተጨማሪም የለንደኑ የቴምስ ወንዝ መታደስ በዙሪያው ያሉ ይዞታዎችን የንግድ ዋጋ ከ10 እስከ 30 በመቶ እንዳሳደገው ሁሉ፣ ይህ የወንዞች ልማትም በአካባቢው ላይ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ መነቃቃትን እንደሚፈጥር ይጠበቃል።
አዲስ አበባ ታሪክንና ተፈጥሮን አጣምራ የጀመረችው የወንዞች ዳርቻ ትራንስፎርሜሽን እጅግ ተስፋ ሰጪ ነው።
ይህም መዲናዋን ቀዳሚ የኢኮኖሚ፣ የሕዝብ ጤና እና የዓለም አቀፍ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ላለው ሥራ ተጨባጭ ማሳያ መሆኑን ያረጋግጣል።
በኪዳኔ በየነ