AMN— ሰኔ 25/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ጋር በመቀናጀት፣ የተፈጥሮ ሀብቶችን እና የዱር እንስሳትን በቴክኖሎጂ ለመከታተልና ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አዲስ አሰራር በይፋ አስጀምሯል።
ይሄው የሳይንስ ውጤት የሆነው የአትላስና የዌብ ዲዛይን መረጃ መስጫ ቴክኖሎጂ፣ በቅድሚያ በባሌ ብሔራዊ ፓርክ እና በስንቅሌ ቆርኪዎች መጠለያ ላይ ተግባራዊ መደረግ ጀምሯል።

የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ስለሺ ግርማ እንደገለጹት ይህ የዲጂታል ሥርዓት የተፈጥሮ ሀብቶችንና የእንስሳትን እንቅስቃሴ በቅርብ በመከታተል ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃን ያደርሳል።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኩመራ ዋቅጅራ ቴክኖሎጂው በሀገሪቱ የመጀመሪያው መሆኑን ጠቅሰው፣ ጥብቅ ስፍራዎችን ይዞታና የአየር ንብረት መረጃን በትክክል በመስጠት ከመሬት አጠቃቀም ረገድ የሚነሱ ተቃርኖዎችን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሰፊ የሆኑትን ጥብቅ ስፍራዎች በሰው ኃይል ብቻ መሸፈን የማይቻል በመሆኑ፣ ቴክኖሎጂው በሰው ሰራሽ አስተውሎት(AI)፣ በሳተላይት፣ በድሮን እና በድብቅ ካሜራዎች ታግዞ የዱር እንስሳትን ደህንነት ይጠብቃል ብለዋል።
በባሌና በስንቅሌ የተጀመረው ዘመናዊ የዲጂታል መረጃ ስርዓት በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሌሎቹም የሀገሪቱ ብሔራዊ ፓርኮች በማስፋት የቱሪዝም ዘርፍን የማስተዋወቅና የማዘመን ስራዎች በስፋት እንደሚከናወኑ በመድረኩ ተበስሯል።
በታምሩ ደምሴ