‘አሸናፊ ትውልድ’ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበራዊ ትስስርን ያጠናከረ ነው – ተሳታፊዎች

You are currently viewing ‘አሸናፊ ትውልድ’ የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበራዊ ትስስርን ያጠናከረ ነው – ተሳታፊዎች

AMN- ሰኔ 28/2018 ዓ.ም

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “አሸናፊ ትውልድ የ5ኪሎ ሜትር” የጉዳና ላይ ሩጫ መርሃ ግብር በተሳካ ሁኔታ ተካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተለያዩ የእድሜ ክልል የተወጣጡ በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሰራተኞች እና ወጣቶች ተሳትፈዋል።

በሩጫው የተሳተፉ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተቋሙ ሠራተኞች እንደገለጹት ዝግጅቱ በከተማዋ ነዋሪዎችና በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ መካከል ቤተሰባዊ ትስስርን የፈጠረ ልዩ ድባብ ነበረው።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ሱልጣን ኡመር የመሳተፍ እድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ የከተማዋን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች በየእለቱ በማቅረብ በአገሪቱ ካሉ ታላላቅ ሚዲያዎች አንዱ መሆን መቻሉን አድንቀዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪም ሚዲያው ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ሴቶች፣ ወጣቶች እና አዛውንቶችን ያካተተ ስራ በመስራቱ መደሰቷን ገልጻለች።

ስፖርት ለጤና ቁልፍ ሚና እንዳለው የጠቀሰው ሚኪያስ የተባለ ተሳታፊ ፣ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ በየትኛውም አካባቢ ለስፖርት እንቅስቃሴ እጅግ ምቹ እና ጋባዥ መሆኗን ጠቁሞ ፣ መንግስት ከወጣቱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራቱ የህዝቡን ጤና እንደሚያሳድገው ገልጿል።

ወርቅነህ ንጋቱ በበኩላቸው ዝግጅቱ በሰራተኞች መካከል ብቻ ሳይሆን ከከተማዋ ወጣቶች ጋር የላቀ ግንኙነትና መስተጋብር እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቁመዋል።

“አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የትውልድ ድምፅ” የሚል መርህ ያለው መሆኑን ያስታወሱት ሌንሳ በቀለ ትውልድ ከሚገነባባቸው ዋና መንገዶች አንዱ ስፖርት በመሆኑ ይህ ሩጫ ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።

ዝግጅቱ አንድነትን እና ሁሉአቀፍነትን የሚያሳይ በመሆኑ ሚዲያው ወደፊትም መሰል ሁነቶችን ማዘጋጀት አጠናክሮ እንደሚቀጥልበት ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ከከተማው ህዝብ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚሰራ የከተማው ሚዲያ መሆኑን የጠቀሱት ሚካኤል ህሩይ ይህ ደግሞ በከተማዋ ላይ ያለውን እምቅ ሀብት ለተቀረው የአለም ህዝብም ይሁን ለኢትዮጵያ ማሕበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ አቅም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በከተማዋ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ለማስተዋወቅ እንደዚህ አይነት ዝግጅቶች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸውም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review