AMN- ሐምሌ 12/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በቀጣዮቹ አምስት አመታት ከ1 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው አዳዲስ የመንገድ ግንባታዎችን ለማከናወን ማቀዱን ገለጸ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ እንደገለጹት፣ የታቀዱት የመንገድ ፕሮጀክቶች አብዛኛዎቹ የዲዛይን ስራቸው የተጠናቀቀ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በጥናት ላይ ይገኛሉ።

ፕሮጀክቶቹ ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ጥያቄ ያነሳባቸው፣ የከተማዋን የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ የሚያሻሽሉ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰቱን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቃልሉ በመሆናቸው ከ2019 ዓ.ም ጀምሮ በበጀት ተደግፈው ወደ ግንባታ ለመግባት ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ከግንባታ ጎን ለጎንም የተገነቡ መሰረተ ልማቶች ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ለህብረተሰቡ ምቹ አገልግሎት እንዲሰጡ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ 1 ሺህ 600 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራ መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
ይህ አፈጻጸም ለረጅም ጊዜ የህብረተሰቡ የቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ ለነበሩ አካባቢዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተጨማሪም ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር 107 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገድ መገንባቱን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት የለውጥ አመታት የከተማዋን የመንገድ አውታር ለማሳደግ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የለውጥ ጉዞው ሲጀመር 6 ሺህ 553 ኪሎ ሜትር የነበረው የመንገድ ሽፋን በአሁኑ ወቅት 8 ሺህ 227 ኪሎ ሜትር መድረሱን ተናግረዋል።
በታደሰ ሽፈራው