በዲጂታል መፍትሔዎች የታጀበው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ምዕራፍ

You are currently viewing በዲጂታል መፍትሔዎች የታጀበው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የፈጠራ ምዕራፍ

AMN- ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም

ልጆችዎ ስልክ ሲጠቀሙ ምን እያዩ እንደሆነ ይጨነቃሉ? በሰፊው የዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ መንገድ ጠፍቶብዎታል? ወይስ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ፍለጋ ተቸግረዋል? አትጨነቁ! የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂዎች ለእነዚህና ለሌሎችም የዘመናችን ፈተናዎች ዘመናዊ ዲጂታል መፍትሔዎችን ይዘው መጥተዋል።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀት ማኅበረሰቡን በሚጠቅም የፈጠራ ሥራ እየቀየሩት ይገኛሉ።

ከዲጂታል ደኅንነት እስከ ዘመናዊ የፓርኪንግ አስተዳደር ድረስ፤ እነዚህ ወጣት ፈጣሪዎች የሀገራችንን የዲጂታል ጉዞ በግንባር ቀደምትነት እየመሩ ነው።

ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ተመራቂ ተማሪዎች መካካል ወጣት ኃይለማርያም አዱኛ የፈጠረው ካስካርድ የተሰኘው የዲጂታል ደኅንነት መተግበሪያ፣ ወላጆች ልጆቻቸው በዲጂታል ዓለም ውስጥ የሚያሳልፉትን ጊዜ እንዲቆጣጠሩ ያስችላቸዋል።

የዚህ መተግበሪያ ልዩ ባህሪ ከልክ ያለፈ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተገቢው መንገድ የሚገታ ሲሆን፣ ከርቀት በመቆጣጠር የልጆችን የስልክ አጠቃቀም መከታተልና የጊዜ ገደብ መጣል ያስችላል።

ሌላው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተመራቂ ተማሪ አዳም ታምራት የፈጠረው ጂኦጂ ካምፓስ ናቪጌተር የተሰኘ መተግበሪያ ሲሆን፣ አዳዲስ ተማሪዎች፣ ሠራተኞች እና ጎብኝዎች በሰፊው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ የሚፈልጉትን ቦታ በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ የሚረዳ ችግር ፈቺ መተግበሪያ ነው።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሌላዋ ተመራቂ ተማሪ ፍሬዘር ገዛኸኝ የሠራችው ኢዝ ስማርት ፓርኪንግ ደግሞ ቴክኖሎጂን የተመረኮዘ ሥርዓት ሲሆን፣ በጎንደር ከተማ የመኪና ማቆሚያ ቦታ ለማግኘት ለሚቸገሩ አሽከርካሪዎች መፍትሔ የሚሰጥ ነው።

ይህ ሥርዓት በአቅራቢያ ያሉ ክፍት ቦታዎችን በቅጽበት በማሳየትና የዋጋ ተመን መረጃን በመስጠት ረገድ ቀዳሚ ነው።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ከንድፈ-ሐሳብ ወደ የንግድ እንቅስቃሴ ለመቀየር ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር ላይ ይገኛል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ተቋሙ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የምርምር ማዕከልን ጨምሮ የተለያዩ የዲጂታል ፕሮግራሞችን በመክፈት፣ ሀገርን በዲጂታል ዘመን ለማሻገር እየሠራ ይገኛል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review