የትግራይን ህዝብ ሰላም የሚነሱ ምርኮኞች

You are currently viewing የትግራይን ህዝብ ሰላም የሚነሱ ምርኮኞች

AMN – ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም

ከስልጣን ፣ ከግልና ከቡድን ጥቅም በስተቀር የህዝቦች አብሮ መኖር ፣ ልማት ፣ ሰላምና የሃገር ሉአላዊነት የማያስጨንቀው ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን ዛሬ ላይ ለሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አልገዛም በማለት ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩን አፍርሶ ሻዕቢያና ግብጽን ከመሰሉ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጎን ተሰልፏል፡፡

ይህ ቡድን የእሱ አምሳያ ከሆኑት ከሻዕቢያና ከግብጽ ጋር ግንባር የፈጠረው የትግራይን ህዝብ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስና የኢትዮጵያን ህዝብ ነጻ ለማውጣትም አይደለም፡፡ ይህ ቡድን ሁለቱ ኃይሎች ኢትዮጵያን የማፈራረስ አላማና ተልዕኮ እንዳላቸው ባለመገንዘቡም አይደለም፡፡

ከ50 አመታት በኋላ ዛሬም ለትግራይ ህዝብ እቆረቆራለሁ ብሎ የአዞ እንባ የሚያነባው ከእሱ በስተቀር የትግራይን ህዝብ በመጨቆን ላይ የሚገኝ ሌላ ቡድን በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለም አይደለም፡፡

ይልቁንም ይህ ቡድን ትናንት በሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ የሚፈጸመ ፤ ህግና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የሞከረ፤ ይህንኑ እኩይ አላማውን ለማስፈጸም ተደጋጋሚ ጦርነት የከፈተ፤ በከፈተው ጦርነት ምክንያት በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ክንድ ተሸንፎ እጅ የሰጠ እና ለፕሪቶሪያው ስምምነት ተገዢ እሆናለሁ ብሎ የፈረመ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላምና ልማት ለማስፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት አስመልክቶ በቅርቡ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸዉ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ መንግስት በሰላም ስምምነቱ መሰረት በትግራይ ክልል ጊዜአዊ አስተዳደር መቋቋሙን አንስተዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት በርካታ አገልግሎቶችን ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች ለአገልግሎት መብቃታቸውን ፤ ቤቶች፤ ሕንጻዎችና የተለያዩ ሃብቶቻቸው ተጠብቀው መቆየታቸውንና መመለሳቸውን፤ ከ60 ሺህ የሚበልጡ የታጠቁ ሃይሎች በመልሶ ማቋቋም አስፈላጊው ክፍያ ተፈጽሞላቸው ከሰራዊቱ እንዲቀነሱ ሙከራ መደረጉን፤ በጦርነቱ የተማረኩ ሰዎችም መፈታታቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ዛሬ የትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪ ነን በማለት፣ የክልሉን ሰላም እና ልማት የሚያደናቅፉትና ህዝቡን የሚያሸብሩት ትናንት በምህረት፣ በይቅርታና በሆደ ሰፊነት የተለቀቁ ምርኮኞች እንጂ ሌላ ቡድን እንዳልሆነ አንስተዋል፡፡

የምርኮኞቹ ሚስቶችና ልጆቻቸው በአብዛኛው አዲስ አበባን ጨምሮ በውጭ ሃገራት እንደሚኖሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አበባ የሚኖሩ ቤተሰቦቻቸውን ያልተነኩበት ዋናው ምክንያት በጥቂት ግለሰቦች ጥፋት ቤተሰብ መታወክ የለበትም፤ ሰላምና ይቅርታ ይሻላል በሚል ሆደ ሰፊነት መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ቡድን የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና የክልሉን ህዝብ የሰላም ጥያቄ ወደ ጎን በመተው ወጣቶችን እያፈሰ ለሱዳን ጦርነት በመሸጥ ላይ የሚገኝ ሲሆን ወጣቶችም በማያውቁት ጦርነት ህይወታቸውን በማጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

ሕገ-ወጡ የህወሃት ቡድን በሚያደርጋቸው ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ህዝቡ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን የችግሩ ገፈት ቀማሽ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በታጠቁ ሃይሎች የሚደረገው ማንኛውም ትግል ህዝብንና ሃገርን የማያሻግር አላማ ቢስ ትግል መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review