AMN- ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም
የለውጡ መንግስት ስኬቶችን ከተቀዳጀባቸው ተግባራት መካከል ማህበራዊ ትስስርን ማጠናከር፣ ሀገር በቀል እሴቶችን ማጎልበት እና የወል ትርክትን መገንባት ዋነኞቹ ናቸው።
ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ብቻቸውን ሀገርን ዘላቂ ሰላም እና ዕድገት ላይ ሊያደርሱ እንደማይችሉ በመገንዘብ፣ የህዝብን ማህበራዊ መሠረት የሚገነቡ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል።
ሀገር በቀል እሴቶች እና የወል ትርክት በማጠናከር እረገድ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ባህላዊ የዕርቅ፣ የንግግር እና የጋራ መኖር እሴቶችን በማስተዋወቅና በማጠናከር ማህበረሰባዊ መረዳዳት እንዲጎለብት ተደርጓል።
ልዩነቶችን እንደ ጸጋ በመቁጠር፣ በጋራ ዕጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ ትርክት እንዲፈጠር ሰፊ የግንዛቤ ሥራዎች ተሠርተዋል።
በተለይም በሀገራዊ ምክክር ህዝባዊ ውይይቶችን በማስፋፋት፣ ያለፉትን አለመግባባቶች በንግግር በመፍታት እና በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ብሔራዊ ንድፍ በመቅረጽ ረገድ ትልቅ ሀገራዊ ስኬት እየተመዘገበበት ይገኛል። ይህም ዜጎች በኢትዮጵያዊነታቸው ላይ ያላቸውን ኩራት እንዲያድግ አድርጓል።
በየዓመቱ የሚከናወኑ የደም ልገሳ፣ አቅመ ደካሞችን መደገፍ፣ የትምህርት ቤት እድሳት እና አረንጓዴ አሻራ እና ማዕድ የማጋራት የበጎ ፈቃድ ስራዎች በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን በማሳተፍ ማህበራዊ ትስስሩን አጠናክረዋል።
በተጨማሪም፣ በተለያዩ ጊዜያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች መድረስ የሚቻልበት ተቋማዊ አሰራር እና ህዝባዊ ንቅናቄ በመፈጠሩ፣ ሰብአዊነት የተሞላበት ባህል ተጠናክሮ ቀጥሏል።
በሪፎርሙ የተገኙት እነዚህ ማህበራዊ ስኬቶች እና የሀገራዊ ምክክር ሂደቶች የኢትዮጵያን ህብረብሔራዊ አንድነት ከመጠበቅ ባለፈ ለሰላም፣ ለልማት እና ለጋራ ዕድገት የማይተካ ሚና አላቸው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ