AMN – ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም.
ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች፣ ሃይማኖቶች፣ ባህሎች፣ ቋንቋዎች እና ማንነቶች መገኛ ስትሆን፣ የሀገሪቱ ምሶሶ የተመሰረተውም በብዝሃነትና በህብረብሔራዊ አንድነት ጽኑ መሰረት ላይ ነው።
የሀገሪቱ የሀገረ መንግስት የግንባታ ሂደት በወል ታሪክ ላይ የተመሰረተ ሲሆን፣ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዚህ የሀገረ መንግስት ግንባታ ውስጥ እኩል እና የላቀ አበርክቶ አላቸው።
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን ይህንን የህዝቦች ወንድማማችነት፣ አብሮነትና አንድነት በመናድ የማይታረቅ የልዩነትና የግጭት ምንጭ ለማድረግ ለረጅም አመታት ሲታክቱ ኖረዋል።
እነዚህ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ጽንፈኝነትን፣ አክራሪነትን፣ ጥላቻን እና ዘረኝነትን የወለዷቸውን ሀገር አፍራሽ፣ ሀሰተኛና ነጠላ ትርክቶችን በማሰራጨት የሀገሪቱን መጻኢ እድል አደጋ ላይ ለመጣል በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል።
የብሔር እና የሃይማኖት ልዩነቶችን እንደ ዋንኛ የግጭት እና የአመጽ ስልት በመጠቀም፣ በህዝቦች መካከል ቅራኔን እና ጥላቻን በማስፋፋት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ ያስመዘገበቻቸውን ስኬታማ ድሎች በአጭር ለመቅጨት ለረጅም አመታት ሞክረዋል።
ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሃይማኖቶች ተከባብረው እና ተቻችለው የሚኖሩባት ሀገር ብትሆንም፣ የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች ግን ይህንን የጋራ እሴት በመናድ ኢትዮጵያ በማይገባት ደረጃ ላይ እንድትገኝ ለዘመናት ታትረዋል።
ብዝሃነትና ህብረ-ብሔራዊ አንድነት የኢትዮጵያውያን ብርቱ ክንድ እና ዐቅም መሆኑን የተረዱት የሀገሪቱ ታሪካዊ ጠላቶች፣ የብሔርና የሃይማኖት ልዩነቶችን በመጠቀም የህዝቦችን ህብረትና አንድነት ለመስበር ለዘመናት ቢጥሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።
የታሪካዊ ጠላቶቻቸውን የጥፋት ተልዕኮ የተረዱት ኢትዮጵያውያንም ልዩነቶቻቸውን በማክበር እና አንድነታቸውን በማጠናከር፣ ብሎም ጽንፈኝነትን እና ዘረኝነትን በመታገል ለዘመናት የቆየውን ወንድማማችነታቸውን እና አንድነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እና ለማደስ ችለዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋ፣ የባህልና የማንነት ልዩነት የግጭት መንስኤ መሆኑ ቀርቶ ኅብር፣ ጌጥ እና የህዝቦች የጥንካሬ ምንጭ ለመሆን በቅቷል።
በዘመናዊው የሀገረ መንግስት የግንባታ ሂደት ውስጥ እንደ ሀገር መክራና ዘክራ የማታውቀው ኢትዮጵያም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገራዊ የምክክር ጉባዔ በማካሄድ የልዩነት ሰንኮፎቿን በምክክር ለመንቀል ወስና ጉዞጀምራለች።
የጠላቶቹን ምኞትና የብዝኃነትን ዐቅም የተረዳው የዛሬው ትውልድም የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን በማድረግ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ የጋራ ዕጣ ፈንታውን በጋራ ተልሟል።
በወንድማገኝ አሰፋ