የህገወጥ ቡድኑ – አፈቀላጤዎች

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

ጽንፈኛው የህወሃት ቡድን ከትናትናዉ ስህተቶቹ ሳይማር ዛሬም ለሌላ ጦርነት እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡

በሃገር ውስጥ እና በውጭ ሃገራት በሚገኙ የክልሉ ተወላጆች፤ ምሁራን፤ ፖለቲከኞችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችም ህገወጥ ቡድኑ እያደረገ ያለው የጦርነት እንቅስቃሴ በማዉገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአሁን በፊት ከህገወጥ ቡድኑ ጎን በመቆም ጦርነት ሲቀሰቅሱ የነበሩ አንዳንድ አክቲቪስቶች፤ ፖለቲከኞችና ዳያስፓራዎች ዛሬ ላይ የጦርነት ዝግጅቱን በተለያዩ መንገዶች በመቃወምና በማዉገዝ ላይ ናቸዉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒዉ ግን ስለ ትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት የማይጨነቁ አንዳንድ የቡድኑ አፈቀላጤዎች ዛሬም ለግል ጥቅማቸዉ ብለዉ የትግራይ ወጣቶችን ለጦርነት በማነሳሳትና በመቀስቀስ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ የህገ- ወጥ ቡድኑ የዲጂታል ሚዲያ ሰራዊቶች የተለያዩ ቋንቋዎችን በመጠቀም ጭምር በተደራጀ መንገድ ጦርነት ይቀሰቅሳሉ፤ ጥላቻን ያባዛሉ፤ ሃሰተኛና የተዛቡ መረጃዎችን ያሰራጫሉ፡፡

ከአሁን በፊት በትግራይ ክልል በተፈጠረዉ ጦርነት ውስጥ ዋንኛ ተዋናይ ሆነው ህዝቡን ለጦርነት ሲቀሰቅሱ የነበሩ እነዚህ የዲጂታል ሚዲያ ሰራዊቶች የክልሉ ሰላምና ልማት ከማደናቀፍ ዉጪ ለህዝቡ ያመጡት አንዳችም ለውጥ የለም፡፡

የህገወጥ ቡድኑ አፈቀላጤዎች ዛሬም እያደረጉት ባለዉ የሚዲያ ዘመቻ የትግራይ ወጣቶች በክልላቸዉ ሰላማዊ ህይወት እንዳኖሩ፤ ከገዛ ክልላቸዉ እንዲፈናቀሉ፤ የጦርነትና የስደት ሰለባ እንዲሆኑ ከማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

መቀሌ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአለም ሃገራት የሚገኙ እነዚህ የጽንፈኛው ቡድን ሚዲያዎችና ተቀላቢ አክቲቪስቶች ወጣቶችን ለጦርነት፤ ለግጭትና ለስደት ከማነሳሳት ዉጪ እነሱ ትናንትም ሆነ ዛሬ አይሞቱም፤ አይቆስሉም፤ አይራቡም፤ አይሰደዱም፡፡

አፈቀላጤዎቹ ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያዊነት ባህል፤ ሃይማኖት፤ ወግና ስርዓት ያፈነገጡ አጸያፊ ቃላትን በመጠቀም ጭምር በወንድማማች ህዝቦች መካከል ጠብ የሚዘሩ ናቸዉ፡፡

እነዚህ የህገወጥ ቡድኑ ተቀላቢ አክቲቪስቶች ጥላቻን፤ ጥርጣሬንና አለመግባባትን ከማባባስ ውጪም ልዩነቶችን በንግግርና በምክክር የመፍታት ባህሉንም ሆነ እዉቀቱን የላቸዉም፡፡

ዛሬም ቢሆን ልዩነቶችን፤ ችግሮችንና አለመግባባቶችን እንደ ወንድማማች ህዝብ በምክክርና በንግግር ከመፍታት ውጪ ጦርነት በመቀስቀስም ሆነ ጦርነትና በግጭት በመፍጠር የሚመጣ አንዳችም መፍትሄ አይኖርም፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review