በጋና አክራ ከተማ የሚገኘውን ታሪካዊውን የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክን ጎብኝተናል – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም

በጋና አክራ ከተማ የሚገኘውን ታሪካዊውን የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክን ጎብኝተናል፤ በሐውልታቸው ሥርም የአበባ ጉንጉን አኑረናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ፤ ስፍራው የጋና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እና የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ እንዲሁም የባለቤታቸው የፋቲያ ንክሩማህ መካነ መቃብርና ታሪካዊ ሙዚየምን ያካተተ ነው ብለዋል።

ጋናውያን ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት አቀንቃኙ መሪያቸው ግዙፍ ሐውልት መታሰቢያ መገንባታቸው የቀደሙትን ማክበር ለትውልድና ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና ያሳያልም ነው ያሉት።

ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማህ ለጋና ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ እንድትወጣ የነበራቸው ራዕይ ዛሬም ድረስ ለትውልዱ ትልቅ የብርታት ምንጭ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ፤ በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ጥብቅ ወዳጅነት እና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) መመስረት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሁልጊዜም በክብር የሚታወስ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review