መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ነው

You are currently viewing መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ነው

AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።

የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ሆለታ በሚገኘው የአካዳሚው ግቢ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች አስመርቋል ።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሃብታሙ፣ ጄኔራል መኮንኖችና የሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ባላት የጂኦ ፖለቲካ አቀማመጥና በተፈጥሮ ሃብቷ ምክንያት ለተለያዩ ፈተናዎች ስትጋለጥ የቆየች ሀገር ናት።

አርበኞች በታሪክ የሀገራቸውን ህልውና በመጠበቅ የተጫወቱትን ሚና በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በልማትና በብልፅግና ጉዞ ላይ መሆኗን የማይወዱ የጥፋት ኃይሎች ሴራና ደባ ለመፈጸም እየሞከሩ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሀገር ፍቅር፣ በአርበኝነትና ሕዝብን የማገልገል ዕሴቶች በመላበስ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚቃጡ የጥፋት ሴራዎችን በብቃት እያመከነ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሚገጥማትን ፈተና በድል ለመወጣት ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ የወል ብቃት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል፡፡

ይሁንና ዘመኑ የሚጠይቀውን የደኅንነት ፈተና ለመመከት የወል ብቃት ብቻ በቂ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ ያለውን አቅም በሰው ኃይል ልማት፣ በትምህርትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም የመከላከያ ሠራዊት የማሰልጠንና የማብቃት ተልዕኮውን በማጠናከር በርካታ የስልጠና ተቋማትን በማስፋፋት የሰው ኃይል ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

በዚህም የሠራዊቱ የሙያ ብቃት፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተልዕኮ አፈጻጸም አቅም እየጎለበተና እየዘመነ መምጣቱን ጠቁመዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review