AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም
ባለፉት 11 ቀናት በየካ ክፍለ ከተማ ሲሰጥ በቆየው የክረምት በጎ ፍቃድ የህክምና አገልግሎት ከ148 ሺህ የሚልቁ ዜጎች ነፃ የህክምና አገልግሎት ማግኘታቸውን የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ገልጿል፡፡
የበጎ ፍቃድ ህክምናው ማጠቃለያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር መገርሳ አለሙ እንደገለፁት ፤ የነፃ ህክምና አገልግሎቱ ከተሰጠባቸው ያለፉት 11 ቀናት የዘጠኙ ቀናት የተጠቃሚዎች ቁጥር መረጃ እንደሚያሳየው ከ148 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል።

የበጎ ፍቃድ ህክምናው በመሰጠቱ ህክምናውን ከወሰዱ ሰዎች መካከል የተወሰኑት የደም ግፊት ፣ የልብ ፣ የማህፀን ጫፍ ካንሰር እና ከአይን ጋር የተያያዙ ህመሞች እንዳሉባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ እንዲያውቁና ወደ ተሻለ ህክምና እንዲሄዱ ማድረግ ስለማስቻሉም ዶ/ር መገርሳ ገልፀዋል።
በተያዘው ክረምት አዲስ አበባን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በበጎ ፍቃድ የህክምና አገልግሎት 20 ሚሊዮን ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን በጤና ሚኒስቴር የህክምና አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ኢሉባቦር ቡኖ ተናግረዋል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው አክለው በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፤ 20 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች ነፃ የቀዶ ህክምና ለመስጠት እና በተለያዩ የህክምና ተቋማት ውስጥ ተበላሽተው የተቀመጡ ሁለት ሺህ የህክምና መሳሪያዎችን ጠግኖ ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በላይሁን ፍስሃ