AMN- ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም
እንግሊዛዊው የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ አንቶኒ ጆሹአ በድራማ የተሞላ ድል አግኝቷል።
የ36 ዓመቱ ቡጢኛ ከአልቤንያው ክሪስቲያን ፕሬንጋ ጋር በሳውዲ አረቢያ ጅዳ ታሪካዊ ፍልሚያ አከናውኗል።
ጆሹአን ከመግጠሙ በፊት አንድ ጊዜ ብቻ የተሸነፈው ፕሬንጋ በቦክሱ ታሪክ ሊዘነጋ የማይችል ታሪክ ለመስራት ተቃርቦ ነበር።
የ35 ዓመቱ ፕሬንጋ በፍልሚያው የመጀመሪያ ዙር ብቻ አንቶኒ ጆሹአን ሁለት ጊዜ ዘርሮታል።

በናይጄሪያ የሁለት ጓደኞቹን ነብስ የቀማ የመኪና አደጋ ከደረሰበት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሪንግ የተመለሰው ጆሹአ ገና በመጀመሪያው ዙር እጅ የሰጠ መሰለ።
ነገር ግን እንደምንም አገግሞ መቼም ከማይመኘው ሽንፈት እራሱን አድኗል። በሁለተኛው ዙር ተጋጣሚው ሊቋቋማቸው ያልቻሉ ቡጡዎችን ሰንዝሮ ዘረረው።
የዕለቱ ዳኛም ክሪስቲያን ፕሬንጋ ከዚህ በላይ መቋቋም አይችልም በሚል ጨዋታውን አቋረጡ ። ጆሹአም ከአሰቃቂ ሽንፈት ወደ ጣፋጭ ድል ተመለሰ። በከባድ ሚዛን ካደረጋቸው 40 ፍልሚያዎችም 36ኛ ድሉን አስመዘገበ።

አንቶኒ ጆሹአ በቀጣይ ከሀገሩ ቦክሰኛ ታይሰን ፊውሪ ጋር የሚያደርገው ፍልሚያ ይጠበቃል። ይህን ፍልሚያ በርካታ የስፖርቱ አድናቂዎች ለዓመታት ሲጠብቁት ቆይተዋል።
ሁለቱ የከባድ ሚዛን ቡጢኞች ፍልሚያው እንዲከናወን የሚያስችል የውል ስምምነት ቢያደርጉም መቼ እና የት የሚለው ግን እስካሁን አልተገለፀም።
በሸዋንግዛው ግርማ