አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ ነው – የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

AMN – ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

አረንጓዴ ዐሻራ የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተጨባጭ ውጤቶች እያመጣ መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፣ የቤተ መንግሥት አስተደደር እና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አመራር እና ሰራተኞች በቆቃ ቤተ መንግሥት አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሀይ ጳውሎስ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ አረንጓዴ ዐሻራ የተጎዱ በርካታ አካባቢዎች መልሰው እንዲያገግሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አዎንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸው፤የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት እንዲሳካ መደላደል መፍጠሩን ተናግረዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የደን ሽፋን እንዲጨምር እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዓለምፀሀይ፤ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል ረገድ ዓለም አቀፋዊ ፋይዳው ከፍ ያለ መሆኑን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የአቮካዶ እና ቡና ችግኞች ተተክለው ለውጤት መብቃታቸውን አስታውሰው፤ይህም የውጭ ምንዛሬ ገቢ እንዲጨምር አስችሏል ብለዋል።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ በበኩላቸው፥ አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ገጽታ እየገነባ መሆኑን ተናግረዋል።

አረንጓዴ አሻራ ቀጣይነት ያለው በመሆኑ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዛሬ ችግኝ የመትከል እና መንከባከብ ስራዎችንን ማጠናከር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review