የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ ይፋዊ ማስጀመርያ መርሃ ግብር ተካሄደ

You are currently viewing የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ ይፋዊ ማስጀመርያ መርሃ ግብር ተካሄደ

AMN- ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም

በባንክ ኦፍ አሜሪካ አጋርነት የሚከናወነው የ2019 ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 10 ኪ.ሜ. ይፋዊ የማስጀመርያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት ተካሂዷል።

በመጪው ዓመት ኅዳር ወር ለሚካሄደው 26ኛው ዙር የታላቁ ሩጫ ውድድር 60 ሺህ ተወዳዳሪዎችን ለማሳተፍ መታቀዱ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

ውድድሩ ሦስት መነሻዎች እንደሚኖሩት የተገለፀ ሲሆን፣ በውድድሩ የ26 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ “ከአንድ ሰዓት በታች እንሮጣለን” በሚል በአረንጓዴው መነሻ ላይ ለሚመዘገቡ ተሳታፊዎች የሰዓት መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ይውላል።

በመድረኩ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ መኪዩ መሐመድ ባደረጉት ንግግር፣ ታላቁ ሩጫ ስፖርትን ባህሉ ያደረገ ማኅበረሰብ በመገንባት ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የታላቁ ሩጫ መስራች ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ በበኩሉ ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ የታላቁ ሩጫ አጋር መሆኑ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጾ፣ ውድድሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለማድረግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም ፣ በተሳታፊዎች የዕድሜ ስብጥር ውስጥ ያለውን ክፍተት ለመሙላት ከጠቅላላው የምዝገባ ቁጥር 5 በመቶ የሚሆነው በነፃ ለተማሪዎች እንደሚመደብ ተገልጿል። የተሳታፊዎች ምዝገባም በቴሌብር እንደሚከናወን ተጠቁሟል።

በአልታየህ ኪዳኔ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review