ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጣለች

AMN ሐምሌ 27/2018

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር አማካኝነት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ማረጋገጧን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

በአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ሀገራዊ ግብ ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ጀምሮ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የብልፅግና ፓርቲ አመራሮችና ሰራተኞች ችግኝ በመትከል አሻራቸውን አኑረዋል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ የተከናወኑ ተግባራት በርካታ ፋይዳዎችን አስገኝተዋል።

መርሃ-ግብሩ ሥነ-ምህዳር እንዲለማና የደን ሀብት ከፍ እንዲል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመው፣ ለዚህ ስኬትም የመላው ኢትዮጵያውያን ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት በአረንጓዴ ዐሻራ ያስመዘገበውን ስኬት በሁሉም ዘርፎች በመድገም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየቀኑ ተስፋን በመትከል የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ያሉት አቶ አደም፣ በቀጣይም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት መጠናቸው እንዲጨምርና ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር፤ የዚህ ዓመት ዘመቻው “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ በመላው ኢትዮጵያ እየተካሄደ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታሪካዊ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በያዝነው ዓመትም ተጨማሪ 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ወደ ሥራ ገብታለች።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review