የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ወጣቶች የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ ገለጹ

AMN – መስከረም 8/2019 ዓ.ም

አዲስ ዓመት መግባቱን ተከትሎ በድምቀት ከሚከበሩትና የኢትዮጵያን ማህበራዊ እና ባህላዊ ገጽታ ከሚያንጸባርቁት ታላላቅ የአደባባይ በዓላት መካከል የደመራ፣ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት ይገኙበታል።

እነዚህ በዓላት ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ሙሉ ዝግጅት አጠናቀዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ወጣቶች፤ በዓላቱን ለማክበር ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ከተማዋ የሚመጡ እንግዶችን በታላቅ የኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል እሴት ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ከወጣቶቹ መካከል ካሳሁን ጉልማ፣ ሰሚራ ኪያር እና አቤል የሺጥላ በዓላቱ ለሀገር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በማንሳት፣ ወጣቶች የእሴቶቹ አስጠባቂ በመሆን የበኩላቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ቆርጠው እንደተነሱ ተናግረዋል።

እነዚህን በዓላት በሰላም እና በድምቀት ለማሳለፍ ይቻል ዘንድ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ጋር በመቀናጀት ከተማ አቀፍ የወጣቶች ኮንፈረንስ አካሂዷል።

በመድረኩም የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ደንድር፤ በዓላቱ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫዎች በመሆናቸው በአብሮነት ልናከብራቸው ይገባል የሚል መልእክት አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶች እና ስፖርት ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ይፍሩ በበኩላቸው፣ በዓላቱ ሲወርድ ሲወራረድ የመጡትን የጥንት ትውፊቶቻቸውን ይዘው በእህትማማችነት፣ በወንድማማችነት እና በፍቅር እንዲያልፉ ወጣቶች ትልቅ ሚና እንዲጫወቱ አሳስበዋል።

በየሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review