AMN- ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አያሌ ታላላቅ ሁነቶችን ፣ የተቀናጁ ህዝባዊ ንቅናቄዎችን እና አስደማሚ የጋራ ስኬቶችን እያስተናገደች ትገኛለች። ትናንት በሀገር አቀፍ ደረጃ መላውን ህዝብ በአንድ ዓላማ ስር ያሰባሰበው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በታሪካችን ውስጥ አዲስ የልማት ምዕራፍ የከፈተ የጋራ ድል ተመዝግቦበታል።

በአንድ ጀምበር 805.3 ሚሊዮን ችግኞችን በመትከል የተመዘገበው ይህ አስደናቂ ውጤት ፣ የ26 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ደማቅ አሻራ ነው።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙ ምን ያህል አቅምና የማድረግ ኃይል እንዳላቸው ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በተግባር ያስመሰከሩበትም ልዩ አጋጣሚ ነው።
ይህ ታሪካዊ ድል እውን ሊሆን የቻለው በአንድ ሀገራዊ ህልም ዙሪያ 26 ሚሊዮን ዜጎች በጋራ በመሰለፋቸው ነው።

ከአዛውንቶች እስከ ህፃናት፣ ከተማው እስከ ገጠሩ፣ ተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ባለሃብቶች ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተሳተፉበት በዚህ ንቅናቄ ፣ ኢትዮጵያውያን አረንጓዴና ለም ኢትዮጵያን ለመገንባት ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
በአንድ ጀምበር የተተከሉት 805.3 ሚሊዮን ችግኞች የሀገሪቱን ዘላቂ ህልውና የሚያረጋግጡ የነገ ተስፋዎች ናቸው።

ከተተከሉት ችግኞች መካከል አብዛኞቹ ለምግብነት የሚያገለግሉ የፍራፍሬ ችግኞችና ዘላቂ የኢኮኖሚ ጥቅም የሚሰጡ የእጸዋት ዝርያዎች በመሆናቸው ለወደፊቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የዜጎችን ገቢ ለማሳደግ ታላቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል።
ዓለም በአየር ንብረት መዛባትና በተለያዩ ፈተናዎች ውስጥ በምትገኝበት በዚህ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ያሳየችው ይህ ታላቅ ስራ ለተፈጥሮ ጥበቃ ዋጋ በመስጠት ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያስመሰከረችበት ነው፡፡

26 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ለተካኪው ትውልድ የተሻለችና የለማች ሀገርን የማስረከብ የሞራልና የታሪክ አደራቸውን ተወጥተዋል።
ትናንት ኢትዮጵያውያን የጋራ ድል ተቀዳጅተዋል ፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ የታየው ተነሳሽነትና ትጋት ኢትዮጵያን ከብልጽግና ጉዞዋ የሚያስቆማት አንዳች መሰናክል እንደማይኖር ማረጋገጫ ሰጥቷል።
የተተከሉ ችግኞችን በጥንቃቄ መንከባከብና ማሳደግ ደግሞ ቀጣዩና ዋናው ኃላፊነት ይሆናል።
በታደሠ ሽፈራው
See less