ከቅድመ-መከላከል እስከ ተጠያቂነት – የመንግሥት የፀረ-ሙስና ዘመቻና የፖለቲካ ቁርጠኝነት

AMN – ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም

መንግሥት በሀገር ሀብት ምዝበራ እና በሕገ-ወጥ ተግባራት ላይ በተሰማሩ አካላት እየወሰዳቸው ያሉ ጠንካራ እርምጃዎች የሕዝብ ወገንተኝነቱን እና የፖለቲካ ቁርጠኝነቱን በተግባር የሚያሳዩ መሆናቸውን የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሰለሞን ተፈራ ገለጹ።

አቶ ሰለሞን ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳመለከቱት፣ መንግሥት ከለውጡ ማግሥት ጀምሮ ሙስና እና ብልሹ አሠራር የሀገር አንድነትና የኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ስጋቶች መሆናቸውን በመለየት የመከላከል እና የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል።

ከለውጡ በፊት የነበረው ሥርዓታዊ ችግር የተደራጀ የፖለቲካ ሙስና የሚታይበት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይዘቱ ተቀይሮ በግለሰቦች እና በተቋማት ደረጃ የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እንደሚስተዋሉ አብራርተዋል።

መንግሥት ይህንን ውስብስብ ችግር ለመግታትም ከቅድመ-መከላከል ባሻገር በወንጀል በተሳተፉ አካላት ላይ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራዎችን አጠናክሮ ቀጥሏል።

በሕገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ በተሳተፉ አካላት ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ የተዘረፈው የሕዝብና የሀገር ሀብት የሚመለስበት ሥርዓት ተዘርግቶ ሥራ ላይ መዋሉን አቶ ሰለሞን ጠቁመዋል።

እነዚህ እርምጃዎች የአመራሩን አስተሳሰብ በመለወጥ፣ ሥልጣንን ለግል ማበልጸጊያ የመጠቀም የቆየ መጥፎ ልማድ እንዲቀንስ አድርጓል ሲሉ አብራርተዋል።

መንግሥት አሠራሮችን ግልጽ ለማድረግ እና የብልሹ አሠራር ቀዳዳዎችን ለመድፈን ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ማዕቀፎች እንዲዘረጉም አድርጓል።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ የተዘረጋው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እና የብሔራዊ መታወቂያ የመሳሰሉት ሙስናን በቴክኖሎጂ ለመግታት የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የሕግ አውጪው፣ ሕግ አስፈጻሚው እና ሕግ ተርጓሚው ተቋማዊ አቅማቸውን በማጠናከር በቅንጅት መሥራታቸው ለፀረ-ሙስና ዘመቻው ውጤታማነት ትልቅ ድርሻ እንዳበረከተም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

ኅብረተሰቡ አገልግሎቶችን በጉቦና በገንዘብ ከማግኘት ተቆጥቦ ሕጋዊ መብቱን እንዲያስከብር እና ከመንግሥት ጋር ቅንጅት በመፍጠር ሌብነትን በንቃት እንዲከላከል አቶ ሰለሞን ጥሪ አስተላልፈዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review