AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ዘመናትን በተሻገሩ አለመግባባቶች እና ልዩነቶች ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር የሰላም፣ የአንድነት እና የልማት አቅጣጫን ለማበጀት ወሳኝ መድረክ መሆኑን የምክክሩ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የምክክር ሂደቱን አስመልክቶ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል አስተያየታቸውን የሰጡ ተመካካሪዎች፤ የኢትዮጵያውያንን ድምጽ በመወከል ሀገራዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየመከርን ነው ብለዋል፡፡
ተመካካሪዎቹ የምክክር ሂደቱ ነጻ እና ገለልተኛ መሆኑን ጠቅሰው ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን ያለምንም ጣልቃገብነት በግልጽ የሚያንጸባርቁበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም ተናግረዋል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ተሳታፊ ሀደ ሲንቄ አረጋሽ ገዳ፤ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች በአንድነት በመሆን አለመግባባቶችን እና ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ሀገራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ በጋራ እየመከሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መመካከር ለጋራ መግባባት መሠረት በመሆን ሰላምን እንደሚያመጣ እና የተለያዩ ሀሳቦችን በማቀራረብ አንድ የማድረግ አቅም እንዳለውም አመላክተዋል፡፡
የምክክሩ ተሳታፊ አቶ አብርሃም ሃይሌ በበኩላቸው፤ ታሪካዊ ስብራቶችን ለመጠገን፣ አለመግባባቶችን በውይይት ፈትቶ ጠንካራ ሀገርን ለትውልድ ለማሸጋገር እና የኢትዮጵያን ክብር ከፍ ለማድረግ የምክክር ሂደቱ የላቀ ፋይዳ እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የምክክሩ ተሳታፊዎች በነጻነት በሚፈልጉት ቋንቋ ሃሳባቸውን እየገለጹ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ አይፈርስም በላይነህ ናቸው፡፡
አቶ አይፈርስም አክለውም ምክክሩ ስኬታማ እንደሚሆን ጠቅሰው፤የሀገሪቱን የዕድገት ከፍታ እና ብልጽግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በምክክር የጸናች ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ የምክክሩ ተሳታፊዎች ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ