AMN-ነሐሴ 14/2018
ኢትዮጵያ ከቀደምት ሥርዓተ-መንግሥታት አንስቶ የረጅም ጊዜ የተቋም ግንባታ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሰላም እና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ሙሉጌታ አየለ (ዶ/ር) ገለጹ።
ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት ተመራማሪው፤ የሀገሪቱ የተቋም ግንባታ ሂደት ከቀደምት ሥርዓተ-መንግሥታት ጀምሮ የቆየ ጥልቅ ታሪክ ያለው መሆኑን አንስተዋል።
በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክም ሲቪል ሰርቪስ፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች እንዲሁም ወታደራዊ እና የደህንነት ተቋማት በሂደት መገንባታቸውን ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ስሙ የሚጠራ ጠንካራ እና አስተማማኝ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።
ባለፉት ዓመታት የመከላከያ ሰራዊት፣ አየር ኃይል እና የጸጥታ ተቋማት በብዙ መልኩ ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አርቴፊሻል ኢንተለጀንሲን (AI) ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑንም ተመራማሪው ጠቁመዋል።
ትውልድ ተሻጋሪ ተቋማትን ለመፍጠር በሂደቱ ውስጥ የመንግሥት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ምሁራንም ያሉ ችግሮችን በመለየትና ምክር ሀሳቦችን በማቅረብ ረገድ የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተመላክቷል።
የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ የደህንነት ተቋማት እና ፍርድ ቤቶች በግለሰቦች ፍላጎት ላይ ሳይሆን በሕግ እና በስርዓት የሚመሩ በመሆናቸው ተቋማዊ ባህልን ማዳበር ለሀገር ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑም ተገልጿል።
«ጥሩ መሪ አንድ ትውልድ ሊያገለግል ይችላል፤ ጠንካራ ተቋም ግንባታ ግን ዘመን ተሻግሮ ሀገርን ያገለግላል» ያሉት ተመራማሪው ሙሉጌታ፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ የተቋም ግንባታዎች ቢኖርም አሁንም ሊጠናከሩ የሚገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን አክለው ገልጸዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ