AMN – ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ሁላችንም ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሀሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ ቆይቶ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል።
የጉባዔው ተመካካሪ ወጣት መርቀኒያ አሊ፤ ጉባዔው እጅግ ስኬታማ፣ አሳታፊ እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የታየበት መሆኑን ተናግራለች።
የምክክር ጉባዔው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሃሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ የምክክር ሂደቱ በመደማመጥ ለሀገር ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የበሰሉ ሀሳቦች የመነጩበት ትልቅ ዕድል ነው ብላለች።
መሰል ሀገራዊ የምክክር ሂደት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ከተደረገ የበለጸገችና ታላቅ ሀገር ለመገንባት ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጸችው።
ሌላኛው ተመካካሪ ተረፈ ተከራይ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሀሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባዔው ቀደም ሲል በሀገሪቱ ለአለመግባባት መንስኤ የነበሩ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመመርመር ዕድል የሰጠ ታሪክዊ ጉባዔ ነው ብለዋል።
የምክክር ሂደቱ እኩል ሀሳብ የመስጠት ዕድል የተረጋገጠበትና አሳታፊ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ጉባዔው መደማመጥ ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ለሀገር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መጠናከር መሰረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ተመካካሪ ሃሊማ ሰይድ ናቸው።
ጉባዔው ተመካካሪዎች የአንዱን ችግር እንደራሳቸው እንዲመለከቱ ዕድል በመፍጠር በጋራ የመፍትሔ ሀሳቦች የተመላከቱበት እንደሆነ መግለጻቸውን ኢዜአ ጠቅሷል፡፡
ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣና የጋራ መግባባትን የሚያጎለብት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።