AMN – ነሐሴ 14/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያውያን የረጅም ዓመታት ተቃርኖን ተቀራርበው በመፍታት፣ በልዩነት ውስጥ አንድነትን በማጉላት ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን እውን ለማድረግ በአንድ ጥላ ሥር ተሰብስበው እየመከሩ ነው።
ይህ ምክክር የሐሳብ የበላይነት በውል የሚታይበት ግልጽ እና መልከ ብዙ ነው።
በአለመመካከር ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ኢትዮጵያውያንም እንደ ሕዝብ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል።
አሁን የተጀመረው የምክክር ጅማሮ የጠብመንጃ አፈሙዝን ላንቃ ዘግቶ የሐሳብን እና የጠረጴዛን ዋጋ ከፍ በማድረግ የሀገርን ተስፋ የሚያስቀጥል፣ የዜጎችንም አብሮነት የሚያጠናክር ሆኗል።
ታዲያ ይህ የሀገር ተስፋ ከኢትዮጵያውያን ፈገግታ ይነበባል።
ምክክሩ ለሀገር ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት የሚውል፣ ሁለንተናዊ ልማቷንም የሚያፋጥን ስለመሆኑ ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉ ተመካካሪዎች ተናግረዋል።
የምክክር ጅማሮው ስኬት ዛሬ ትውልድ ውስጥ የሚጻፍ፣ ለነገ ትውልድም ስንቅ እና ተስፋን የሚያጭር ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ መጪው ትውልድ በመቀራረብ እና በመመካከር የሚያምን፣ ደግሞም ለሀሳብ የበላይነት ይገዛ ዘንድ በር የሚከፍት ነው ብለዋል።
በተመስገን ይመር