AMN- ነሐሴ 21/2018 ዓ.ም

የትውልድ ድምጽ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በከተማዋ የተሰሩ ሁሉን አቀፍ ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ላበረከተው አስተዋጽኦ ከአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት እውቅና ተሰጠው።
ኤ ኤም ኤን ባለፉት አምስት አመታት በከተማዋ የተመዘገቡ የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ስራዎች በህዝቡ ተደግፈው ስኬታማ እንዲሆኑ በሚዲያ አማራጮቹ በሰራቸው የይዘት ስራዎች ነው ምክር ቤቱ እውቅና የሰጠው።
በወቅቱም የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ቡዜና አልከድር፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የህብረተሰቡ አቤቱታ ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ትልቅ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰለሞን ዲባባ የተቋማቸውን እውቅና በተቀበሉበት ወቅት እንደገለጹት፤ ሚዲያው በየጊዜው በይዘት፣ በፈጠራና በመረጃ ተደራሽነት እያሳየ ያለው ለውጥ የህዝቡን የለውጥና የመልማት ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ነው።
የአሁኑ እውቅናም ሚዲያውን ለተሻለ ትጋት የሚያነሳሳና ለቀጣይ የህዝቡን አዳጊ የልማት ፍላጎትና የመረጃ እርካታን ይበልጥ ለማላቅ ስንቅ የሚሆን ነው ብለዋል።
በደሴ ብርሃኑ