AMN – ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግና በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታዩ የግንዛቤ ውስንነቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል የተቀናጀ አሰራር እንደሚዘረጋ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት እና የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎቶች ኤጀንሲ፤ የባለድርሻ አካላትና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች በተገኙበት የውይይት መድረክ አዘጋጅተዋል።

በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተፈራ ሞላ (ዶ/ር) ፣ በተለይም በጋብቻ እና በሞት ምዝገባ ሂደቶች ላይ ጉልህ የሆኑ የግንዛቤ ክፍተቶችና የአሰራር ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
እነዚህን ክፍተቶች በዘላቂነት ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በጋራና በቅርርብ መስራት አሁን ላይ ሊዘገይ የማይገባው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ዶ/ር ተፈራ ጠቁመው፤ የተሟላና የተቀናጀ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት ከተማዋ ስማርት ሲቲ ለመሆን የምታደርገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያፋጥነው ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የኢትዮጵያን የሲቪል ምዝገባና የነዋሪነት አገልግሎት ጅማሮ እንዲሁም አሁን የደረሰበትን ደረጃ የሚዳስስ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በሃይሉ አያሌው