AMN -ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ ኢትዮጵያን የሁለንተናዊ ብልጽግና አብነት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የኢንዱስትሪው ዘርፍ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
አቶ ጃንጥራር ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ዘርፉ በስራ እድል ፈጠራ፣ በኤክስፖርት፣ በገበያ ትስስር፣ በማክሮ ኢኮኖሚ እና በማምረት አቅም እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት የኢኮኖሚ ሞተር መሆኑን ጠቁመዋል።
ኃላፊው አያይዘውም ከእንድስትሪዎች የሚጠበቀውን ውጤት ለማግኘት የአመራር ድጋፍ መስጠት፣ የቦታና የገበያ ትስስር ችግሮችን መፍታት እንዲሁም የመሰረተ ልማት እና የግብዓት አቅርቦቶችን ማመቻቸት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በቀጣይ ለሚከበሩት የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላት አምራች ኢንዱስትሪዎች አስፈላጊውን የኢንዱስትሪ ምርት በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ህብረተሰቡን ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማስተናገድም በየክፍለ ከተማው የበዓላት ባዛሮች በመዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊው አቶ ጃንጥራር አባይ አስታውቀዋል።
የክፍለ ከተማ የኢንዱስትሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ባለፉት ወራት የአምራቾችን የብድር፣ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራትና የገበያ ትስስር ችግሮች በመለየት ከአስተዳደሩና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በርካታ የመፍትሔ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ በተወሰዱ አወንታዊ እርምጃዎች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ አምራቾችን ቁጥር እንዲጨመርና በርካታ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ማስቻሉም ተመላክቷል።
በአስማረ መኮንን