ሌብነትና ብክነትን ለማስወገድ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ርምጃ እየተወሰደ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ የሌብነትና የብክነት ችግሮችን ለማስወገድ አስተዳደሩ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች የከተማ አስተዳደሩ የ5 ዓመት ዕቅድና የ2019 በጀት ዓመት ውይይት ማጠቃለያ በስጡት የሥራ መመሪያ ፣ የከተማ አስተዳደሩ ሌብነትንና ብክነትን በመታገል ህዝብን በታማኝነት ለማገልገል ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡

ከንቲባዋ የሚስተዋሉ የሌብነትና የብክነት ችግሮች በአብዛኛው ከጉቦኝነት አስተሳሰብና ስር ከሰደደ ልምምድ ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

እነዚህን ችግሮች ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ አስተዳደሩ በተጨባጭ ማስረጃ ላይ የተመሰረተ ጠንካራና ድርድር የለሽ ርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ከቅጣት ባለፈም አሰራርን በቴክኖሎጂ ማዘመን፣ የበጀትና የጊዜ ብክነትን ማስወገድና የህዝብ ተሳትፎን ማሳደግ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት አቅዶ በተመደበላቸው በጀትና ጊዜ ውስጥ የመጨረስ ብቃትና ልምድ ማደጉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፣ አስተዳደሩ የበጀት ቁጥጥር በማድረጉ ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ማሳካት መቻሉን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግና አገልጋይነትን ለማረጋገጥ በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንደሚቀርበው “ዋርካ” መሰናዶን የመሰሉ የህዝብ መድረኮች እንዲመቻቹ መደረጉን ጠቅሰዋል።

ይህም ህዝቡ አስተዳደሩን ነፃ ሆኖ እንዲተችና እንዲጠይቅ መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል፡፡

የኦዲት ግድፈቶችን በኦዲት ፎረሞች በመገምገም ኃላፊዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያስተካክሉ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

እነዚህ የተከናወኑ የመልካም አስተዳደርና የአሰራር ማሻሻያ ስራዎች አስተዳደሩ ብክነት እንዳይኖር ያለውን ጽኑ ፍላጎትና ህዝብን በታማኝነት የማገልገል ቁርጠኝነት የሚያሳዩና ለቀጣይ ዕቅዶች ስኬትም ዋና መሰረት መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስገንዝበዋል።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review