AMN- ነሐሴ 26/2018 ዓ.ም

በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታየ ባለው የጂኦፖለቲካ ውጥረት ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ደህንነቷን መሠረት ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እየተከተለች መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ጋሻው አይፈራም(ዶ/ር) ገለጹ።
ጋሻው አይፈራም(ዶ/ር) ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሰንኮፍ መሰናዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ወቅታዊውን ዓለም አቀፍ የጂኦፖለቲካ ውጥረት እና የኢትዮጵያን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አሁን ላይ ያለው የዓለም የጂኦፖለቲካ ውጥረት በአብዛኛው በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣ በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እና ለእነኚህ ቴክኖሎጂዎች የሆኑ ወሳኝ ግብዓቶች እንዲሁም ባህር እና መሬት ላይ ያሉ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመቆጣጠር ዙሪያ ያተኮረ ፉክክር የሚታይበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ዓለም ከአንድ ዋልታ ወደ ብዙ ዋልታ እያደረገ ባለው ሽግግር ውስጥ ትገኛለች ያሉት ጋሻው(ዶ/ር) ፤ ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ወደ አንዱ ኃይል ወይም ጎራ የማመዘን ፖሊሲ አታራምድም ብለዋል።
ሀገሪቱ ከምስራቅም ሆነ ከምዕራብ ዓለም ከሚገኙ አካላት ጋር ብሔራዊ እና የደህንነት ጥቅሟን መሠረት ያደረገ አውዳዊ ግንኙነት ትመሰርታለች ብለዋል ።

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተና ቀጠናውን ወደ ሰላምና ውህደት ሊያመራ የሚችል ቅኝት ያለው መሆኑን ያብራሩት ዳይሬክተር ጀነራሉ ፤ የባህር በር ጥያቄው ኢትዮጵያ ከነበራት ታሪካዊ ስልጣኔና ትስስር አንፃር እንደገና የማስታረቅ ሂደት ተደርጎ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመስረት፣ የባህር በር ፍላጐቷን ሌሎች አካላት እንዲረዱት የማድረግና ወደ ድርድር የማምጣት የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ትገኛለች ብለዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ