AMN -ነሐሴ 27/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን በከተማዋ የተገነቡትን ዘመናዊና ምናባዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስተዋወቅ፣ በዲጂል የተደገፉ የአገልግሎት ተቋማትን በማብቃትና በመቆጣጠር ረገድ ከፍተኛ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል።
ኮሚሽኑ የመዲናዋን የልማት ገጽታዎች ለማስተዋወቅ ያለመ አዲስ መርሃ-ግብር በመንደፍ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በመዲናዋ የሚገኙ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም መሰረት የእኛ ፋሚሊ የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ስር የሚገኙ አረጋውያን አዲስ የተገነቡት የከተማዋ የቱሪስት መዳረሻዎችን የጉብኝት መርሃ ግብር አካሂደዋል፡፡

በጉብኝቱ መርሃ-ግብር ላይ የተሳተፉት አረጋዊያን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት፣ የከተማዋን የሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ልማት ውጤቶችን ተንከባክቦ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ ገልጸው፤ አዲስ አበባ አሁን ላይ ከበለጸጉት የዓለም ከተሞች ጋር አቻ መሆኗን ተናግረዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት አረጋዊ መኮንነ ደጋዴ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው ልማት እጅግ አስገራሚ፣ ለመግለጽም የሚከብድ፣ በቴክኖሎጂና በውበት የታጀበ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እኔም ምነው ወጣት ሆኜ በዚህ በአማረና በተዋበ የልማት ሰራ ተከፍየ አሻራየን ባስቀመጥኩ ነበር በማለትም የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ጉብኝ አረጋዊ ሊዮን ጴጥሮስ በበኩላቸው፣ ጉብኝት ያደረጉበትን አካባቢ ከዚህ በፊት ያውቁት እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን በአዩት የልማት ሰራ መደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ያየሁት የልማት ሰራ ከዚህ በፊት የማውቀው አካባቢ ሳይሆን ዉጭ አገር የገባሁ ነው የመሰለኝ ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
አረጋዊያኑ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙትን የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ያደረጋቸው የእኛ ፋሚሊ የአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ቴክኒካል ማናጀር አቶ ዳባ ቱፋ በበኩላቸው፤ አባቶቻችን በህይወት ዘመናቸው አገራቸውንና ህዝባቸውን ሲያገለግሉ የቆዩ በመሆናቸው፣ አሁን የተገነቡትን ዘመናዊ የከተማዋን የልማት ስራዎችና የወደፊት ራእዮች እንዲጎበኙ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አባቶቻችን ይህችን ሀገር በአቅማቸው ያቆዩልን ናቸው ያሉት አቶ ዳባ፣ ዛሬ ደግሞ እጅግ የዘመነችውንና ያማረችውን አዲስ አበባን አይተው ተስፋቸውን እንዲያድሱና እንዲደሰቱ አድርገናቸዋል ብለዋል።
አቶ ዳባ አክለውም፣ ድሮ ቆሻሻና ወንጀል ይበዛበት የነበረው አካባቢ ዛሬ ለዘመናዊ ውበትና ለላቀ ቴክኖሎጂ በመብቃቱ በጣም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን የቡድን መሪ አቶ አማኑኤል ባቡ በበኩላቸው፣ የመዲናዋ አዳዲስ የቱሪዝም ውጤቶች የሀገር ውስጥና የዓለም አቀፍ ጎብኚዎችን ቀልብ እየሳቡ መሆናቸውን ገልጸው፣ የጉብኝቱ አላማም እነዚህን ዘመናዊ የቱሪዝም መዳረሻዎች በስፋት ማስተዋወቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
አቶ አማኑኤል አክለውም፣ አረጋዊያን በጉብኝታቸው ከዚህ ቀደም የሚያውቋትን አዲስ አበባ እና አሁን የደረሰችበትን የእድገት ደረጃ ሲያነጻጽሩ በጣም መደነቃቸውን እና አዳዲሶቹን የስማርት ኮሪደሮች፣ የፓርኮች፣ የዲጂታል ሙዚየሞችና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ሲያዩ በጣም ተደንቀዋል ብለዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊ አረጋዊያን በውጭ ሀገር ለሚኖሩ ዘመዶቻቸው አዲሷን አዲስ አበባ መጥተው እንዲጎበኙ ጥሪ እንደሚያስተላልፉም ቃል መግባታቸው ተመላክቷል፡፡
በአስማረ መኮንን