የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የፕሬስ መግለጫ

እንኳን ለጳጉሜን 2 የማንሰራራት ቀን አደረሳችሁ፣ አደረሰን!

ኢትዮጵያ የብልጽግና ትልሞቿን በፅኑ መሠረት እየገነባች ነው፡፡ ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት ፖሊሲዎች እና ዕቅዶች እየተመራች ለኹለንተናዊ ብልጽግና እየተጋች ትገኛለች፡፡ በየዘመን አንጓዉ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በተደመረ ዐቅም እየተሻገረች፤ ከችግሮች እና ፈተናዎች ዕድሎችን መንጭቃ እያወጣች፤ ነገዋን በጠንካራ መሠረት ላይ እያጸናች ነው፡፡

ለዘመናት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ከዓድማስ እስከ ዓድማስ የሚያውለበልበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ነገዉን ታሳቢ አድርጎ እንደ ቢሾፍቱ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባሉ መሠረተ ልማቶች እና ኹለንተናዊ ለውጦች ውስጥ እያለፈ ነው፡፡ ፡፡ ነባር እና ዐዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች እየለሙ እና ተደራሽነታቸዉ እያደገ ነው፡፡ ግብርናችን ከዝናብ ጥገኝነት እየተላቀቀ እና የገጠሩም የከተሜዉም የሥራ ዕድል እየኾነ ነው፡፡ የታዳሽ ኃይል አማራጮቻችን ከውኃ፣ ከነፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከጂኦተርማል እና ከኑክሊየር ኃይል እንዲኾኑ የመደመር መንግሥት ሌት ተቀን እየሠራ ነው፡፡

ከተሞቿ ጎስቋላ ገጽታቸዉ እየተቀየረ እና ነገን እየዋጁ፤ መሠረተ ልማቶቿ እየተስፋፉ እና እየተቀናጁ፤ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ዐቅሟ እየተጠናከረ፤ የቀጣናዉ የታዳሽ ኃይል ማእከልነቷ እያደገ፤ የማዕድን ሀብቶቿን በላቀ ደረጃ ጥቅም ላይ እያዋለች ለመጪዉ ትውልድ ኹለንተናዊ ብለጽግና እየሠራች ነው፡፡

የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያበስሩ፤ እመርታዊ ዕድገቷን የሚያፋጥኑ ፅኑ መሠረቶች ላይ እየተገነቡ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ሥርዐቱን ለማጽናት እና መሻታቸዉን እውን ለማድረግ ያላቸዉን ቁርጠኝነት በመንግሥት ጥሪዎች በሚያሳዩዋቸው ተሳትፎዎች እየገለጹ ነው፡፡

በ7ኛዉ ጠቅላላ ምርጫ ከሌሊት እስከ ሌሊት ፈተናዎችን ተቋቁመዉ ድምፅ መስጠታቸዉ እና ውጤቱን በደስታ መቀበላቸው፤ በአረንጓዴ ዐሻራ በየዓመቱ እያደገ የመጣ ተሳትፎ እና ስኬት ማስመዝገባቸው፤ የልዩነት ሐሳቦችን በሰላማዊ መንገድ ለመግራት ሀገራዊ ምክክርን መምረጣቸው ኢትዮጵያውያን በመደመር መንግሥት ትልሞች ላይ የያዙትን የጋራ ተስፋ እና ለስኬቱም እያደረጉ ያለዉን ርብርብ የሚያሳይ ነው፡፡

የዴሞክራሲ ሥርዐትን በማንበር፤ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመከተል፤ የከተሞችን ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤ ወደ ገጠር በማላመድ፤ የታዳሽ ኃይል አቅርቦትን በመሻሻል፤ የትራንስፖርት መሠረተ ልማቱን በማዘመንና በማስፋፋት ለኢትዮጵያ ኹለንተናዊ ብልጸግና ፅኑ መሠረት እየተቀመጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጳጒሜን 2ን “የማንሰራራት ቀን” በሚል ስያሜ እያከበርን የምንገኘው፡፡

ጳጒሜን 2 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review