AMN – ጳጉሜን 3/2018 ዓ/ም
ከሀገር ዳር ድንበር እኩል የፀና፣ ለቃሉም የታመነ የፅናት ማሳያ የሆነው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ገድል ተነግሮ እና ተዘርዝሮ የማያልቅ ነው።
“ወጥቶ አደር” ለምን? የሀገርን ዳር ድንበር ማስከበር እና የህዝብን ክብር መጠበቅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰርክ ተግባሩ ነው።
የተፈጥሮ የአየር ሚዛን የማይበግረው፣ በድቅድቅ ጨለማ ለሀገሩ በዱር ገደል የሚያድር፣ በቀን ሀሩር የሀገሩን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ሁሌም በተጠንቀቅ የሚሰለፍ ሰራዊት ነው።
ዳገትን የሚወጣ፣ ሲሻው ቁልቁለትን የሚወርድ፣ ሜዳን የሚያካልል፣ አለፍ ሲልም ወንዝን የሚሰነጥቅ – ይህ ሁሉ የሚሆነው እና የሚያደርገው ለሀገር ዳር ድንበር መከበር ሲባል ነው።
መከላከያ ሰራዊት ባለፉት አመታት ራሱን ለማዘመን ዘርፈ ብዙ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየ ሲሆን፤ ዘመናዊ ትጥቅን ከብቁ የሰው ሃይል ጋር አቀናጅቷል።
በመሬት ጠበብቶች እግረኛ ጦርን ከሜካናይዝድ ትጥቅ ጋር አዋዶ የሀገርን ምሉዕነትን ይጠብቃል።
“አየሩ የኛ ነው” በሚል መርህ አለም አቀፍ ምጥቀትን እና ውስብስብ ቴክኖሎጂን የታጠቁ የጦር ጀቶችን እና አየር ላይ እንዳሻቸው የሚቀዝፉ አብራሪዎችን ዝግጁ አድርጎ የሀገርን የአየር ክልል ይጠብቃል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ከቀን ባለፈ በምሽት የሀገርን የአየር ክልል በብቃት የመጠበቅ አቅም ያልነበራቸው የጦር ጀቶች ዛሬ ላይ ለ24 ሰዓት በአየር የሚያነፈንፉ፣ በሀገር ጠላት ላይም እሳት በሚተፉ ጀቶች ተተክተዋል።
ወዲህ ደግሞ ስመ ገናናው የባህር ሃይል ከተበተነበት አሰራሩ ተላቆ ነፍስ ዘርቶ ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን አስቦ ተደራጅቷል።
ታዲያ ተቋሙ ባለፉት አመታት ያደረጋቸው ሪፎርሞች ተቋሙን በጠንካራ አለት ላይ የሚያቆሙ፣ የትናንት ጽናቱን ለነገም ይደግመው ዘንድ የሚያደርጉ ትላልቅ እርምጃዎች ናቸው።
በተመስገን ይመር