የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ከዘመኑ የሚወዳጅና ፈተናን በብቃት መመከት የሚችል ተቋማዊ ቁመና ሊኖረው ይገባል

You are currently viewing የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ከዘመኑ የሚወዳጅና ፈተናን በብቃት መመከት የሚችል ተቋማዊ ቁመና ሊኖረው ይገባል

AMN – ሚያዝያ 7/2018 ዓ.ም

በፍጥነት እየተለዋወጠ የመጣውን ዓለም አቀፋዊ ሁኔታ ለመመከትና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም በላቀ ደረጃ ለማስጠበቅ፣ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ብቁ ተቋማዊ ቁመና መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚተገበር ተቋማዊ የሰው ሀብት ልማት ማሻሻያ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት፤ ሀገርን ለበርካታ አስርት ዓመታት በጽናት ያገለገለው የውጭ ግንኙነት ዘርፍ፣ አሁን ላይ አቅምና ብቃትን አብዝቶ የሚሻበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል።

ሚኒስቴሩ ሀገር ከምትጠብቀው ውጤትና ዓለም ከደረሰችበት የዲፕሎማሲ ከፍታ አንጻር የቤት ስራዎቹን በብቃት መወጣት እንዲችል የተሟላ ሪፎርም እየተገበረ መሆኑንም አውስተዋል።

ወቅቱ ከተቋማዊ ግንባታ በበለጠ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ ዲፕሎማቶችን ማሰማራትን እንደሚጠይቅ ሚኒስትሩ ገልጸው፤ አዲሱ የሰው ሀብት ልማት ፕሮግራም እንዲሳካ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እንደሚደረግም አረጋግጠዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርሃኑ ጸጋዬ በበኩላቸው፤ አንጋፋው የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ካለው የታሪክ ድርሻ አንጻር በሚጠበቅበት የብቃት ደረጃ ላይ ሳይገኝ መቆየቱን አንስተዋል።

የአመራር ብቃትና ተለዋዋጭነት ማነስ፣ በቆይታ ላይ ብቻ የተመሰረተ የስምሪት ሥርዓት፣ ወጥ የሆነ የሠራተኛ ምዘና አለመኖር፣ አገልግሎት አሰጣጥን በቴክኖሎጂ አለማስደገፍ እና ምቹ ያልሆነ የሥራ አካባቢ በጥናት ከተለዩ መፍትሔ ፈላጊ ችግሮች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

እነዚህን ዘመን የተሻገሩ ተግዳሮቶችን በመፍታት ቀልጣፋና ንቁ አሠራርን ለማስፈን የሪፎርሙ ሚና የላቀ መሆኑን አምባሳደሩ አስታውቀዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ይፋ ያደረገው አዲሱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ሀገሪቱ ለሰላምና ለቀጣናዊ ብልጽግና ያላትን ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ሲሆን፤ አዲሱ ተቋማዊ ማሻሻያም ለዚሁ ፖሊሲ ስኬታማነት እንደ ዋነኛ መሣሪያ እንደሚያገለግል ተገልጿል።

በአቡ ቻሌ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review