አውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዛሬ በሚከናወኑ ስድስት ጨዋታዎች ይጀምራል

AMN-ጳጉሜን 3/2018 ዓ.ም

የ2026/27 የውድድር ዘመን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ዛሬ በይፋ ይጀምራል። በሊግ ፎርማት መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ ሦስተኛ ዓመቱን የሚይዘው የዓለማችን ትልቁ የእግርኳስ መድረክ ዛሬ ጅማሮውን ሲያበስር ስድስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።

ሪያል ማድሪድ አንተር ሚላንን በሳንቲያጎ ቤርናቢዩ የሚያስተናግድበት ፍልሚያ የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ጨዋታው ዳግም ሪያል ማድሪድን ለተረከቡት ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆ የተለየ ስሜት አለው።

ጆዜ ለኢንተር ሚላን ያላቸው ፍቅር አሁንም ድረስ ያልበረደ ነው። የ63 ዓመቱ አሰልጣኝ ኢንተርን በመሩበት ሁለት የውድድር ዓመት ስኬታማ ጊዜ አሳልፈዋል። በ2010 ያሳኩት የሦስትዮሽ ድል በጣልያን እግርኳስ የኢንተር ሚላን ታሪክ ብቻ ሆኖ አሁንም በክብር ተቀምጧል።

ጆዜ የሦስትዮሽ ድል ባለቤት እንዲሆኑ የረዳቸው እና የቀድሞ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቻቸው ክሪስቲያን ኪቩ ኢንተርን በአሰልጣኝነት እየመራ ይገኛል። ሩማኒያዊውን አሰልጣኝ ማግኘትም ለጆዜ ሌላው ልዩ አጋጣሚ ነው።

አስገራሚው ነገር የሦስትዮሽ ድል ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻላቸውን የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ባየርን ሙኒክን 2ለ0 በማሸነፍ ያነሱት ዛሬ በሚጫወቱበት ሳንቲያጎ ቤርናቢዩ ላይ ነበር። ለኪቩም ሌላ ትውስታ የሚቀሰቅስ አጋጣሚ ይሆናል።

በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ኢንተር ሚላን ለቆ ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ዴንዘል ዱምፍሪስ ገና በመጀመሪያ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታው የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ ይገጥማል።

በሜዳ ላይ ፍልሚያ ማድሪድ ከያዛቸው የተጫዋቾች ጥራት አንፃር የማሸነፍ ግምቱን ወስዷል። በስፔን ላሊጋ አራተኛ ሳምንት በሪያል ቤቲስ የተሸነፈው ማድሪድ የዛሬው ጨዋታ ዳጋፊዎቹን የሚክስበት ጥሩ አጋጣሚ ይመስላል።

ያለፈው ዓመት የሴሪ አው ባለድል ኢንተር ዘንድሮም የሊግ ጅማሮው አስደናቂ ነው። ሦስቱንም ጨዋታዎች ድል በማድረግ ጥንካሬውን እያሳየ ይገኛል።

በሁለቱ ክለቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት የስፔኑ ክለብ የሃይል ሚዛኑን ይወስዳል። ማድሪድ ኢንተርን በገጠመባቸው ሰባት የመጨረሻ ጨዋታ ስድስቱን አሸንፎ በአንዱ ብቻ እጅ ሰጥቷል።

ዛሬ ምሽት 4:00 የሚጀምረው ጨዋታስ የማድሪድን የበላይነት ያስቀጥላል ወይስ ኢንተር ያሸንፋል?

በሌሎች ጨዋታዎች የእንግሊዙ ክለብ ማንችስተር ሲቲ ወደ ፖርቹጋል አቅንቶ በስታዲዮ ዶ ድራጋኦ ፖርቶን ምሽት 4:00 ይገጥማል። በተመሳሳይ ሰዓት ሊል ከ ሪያል ቤቲስ ፤ ቦሩሲያ ዶርትመንድ ከ ቪያሪያል ይጫወታሉ።

ኤኢኬ አቴንስ ከ ላስክ እንዲሁም ክለብ ብሩጅ ከ አስቶን ቪላ ደግሞ በተመሳሳይ 1:45 ላይ ከሌሎቹ ቀድመው ጨዋታቸውን ይጀምራሉ።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review