ገንዘብ እየተቀበለ ያለ ወረፋ ነዳጅ ሲያስቀዳ የነበረ የማደያ ስራ አስኪያጅ ከ3 ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

You are currently viewing ገንዘብ እየተቀበለ ያለ ወረፋ ነዳጅ ሲያስቀዳ የነበረ የማደያ ስራ አስኪያጅ ከ3 ግብረ አበሮቹ ጋር በቁጥጥር ስር ዋለ

AMN ሚያዝያ 21 ቀን 2018 ዓ/ም

የወንጀል ድርጊቱ የተፈፀመው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ቱሉ ዲምቱ አካባቢ ከሚገኝ አንድ ማደያ ውስጥ ነው።

ተጠርጣሪዎቹ በተጠቀሰው አካባቢ ከሚገኘው ነዳጅ ማደያ ስራ አስኪያጅ ከሆነው ቴዎድሮስ ሻምበል ጋር በመመሳጠር ኮድ 3 ኢት 75883 አይቪኮ ትራከር የጭነት አሽከርካሪ የሆነው ብርሀን መለሰ ያለ ወረፋ ነዳጅ እንዲቀዳ በደላላው ያሬድ ዓለምሰገድ በኩል ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ።

ይህንን የወንጀል ተግባር ለመፈፀምም ከሌሊቱ 9፡30 ሠዓት ላይ እንዲመጣ እና ለዚህ ክፍያ 30 ሺህ ብር ለስራ አስኪያጁ እንዲሰጥ በደላላው በኩል ተወስኖ በቀጠሮ ይለያያሉ።

የወንጀል ድርጊቱ መረጃ የደረሰው የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተል ቆይቶ በተባለው ሠዓት አሽከርካሪው ያለ ወረፋ እና ያለ ኩፖን ነዳጁን ሊቀዳ ገንዘቡን ለወንጀል ድርጊቱ ተባባሪ ለሆነው አንድ የመኪና ጥበቃ ስራ ላይ ለተሰማራ ሚሊዮን ከበደ ለተባለ ግለሰብ በመስጠት ገንዘቡን ሲቀባበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡

ከፍተኛ የሀገር ሀብት ወጥቶበት በድጎማ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባውን ነዳጅ በህገ ወጥ መንገድ በመጠቀም ሀገርን ለምዝበራ የሚዳርጉ የማደያ ባለቤቶች እና ሰራተኞች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ከማደያ ነዳጅ በመቅዳት መልሰው የሚሸጡ ግለሰቦች ጭምር በመኖራቸው ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አሳስቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review