AMN – ጳጉሜን 4/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ኢትዮጵያ በሀገር በቀል እሴቶቿ፤ የነገውን ብሩህ ተስፋዋን በገዛ እጆቿ እየቀረጸች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው በትውልድ ቅብብሎሽ ያገኘናቸውን ድንቅ የሀገር በቀል እሴቶቻችንን በማጎልበት እና በመደመር ፍልስፍና በመመራት፣ ለጽኑ ኅብረብሔራዊ አንድነታችን የማይናወጥ መሠረት ጥለናል ነው ያሉት፡፡
ታሪካዊውን ሀገራዊ ምክክር የመጀመር የታሪክ እጥፋት ተነስተን፣ የሁሉም ዜጎቻችንን ሕይወት ከሚለውጡ ሰው-ተኮር የኮሪደር ልማታችን፣ የበጎ ፈቃድ ስራዎቻችን እንዲሁም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብርን በተግባር እውን እስከማድረግ ድረስ፤ ሁላችንም በአንድነት ስንቆም የጋራ ትርክቶቻችን ወደ ጋራ ስኬት እንደሚያሻግሩን በተግባር አሳይተናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እኛ የምንገነባው አካታች የሆነች፣ በኢኮኖሚ ራሷን የቻለች፣ የአብሮነትና መረዳዳት ባህል የጎለበተባት ጠንካራ ሀገር ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ኢትዮጵያውያን የጋራ ታላቅነትና እምቅ አቅም በተግባር እያረጋገጥን እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድነት ወደ ብልጽግና ጉዟችን እንቀጥላለን፤አንድ ህዝብ፣ ታላቅ ሀገር ኢትዮጵያ! ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡