AMN – መስከረም 22/2019
እሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት፣ ኢትዮጵያውያን በህብር የሚደምቁበት የሰላም፣ የፍቅር እና የይቅርታ በዓል ነው።
ክረምቱ አልፎ በጋው ሲመጣ፣ ጨለማው ተገፎ ብርሃኑ ሲበራ የሚከበረው፣ ጥልቅ ባህላዊ እና መንፈሳዊ እሴቶች ያሉት ይህ በዓል የተፈጥሮን መታደስ ብቻ ሳይሆን የሰዎችን የልብ መታደስ እና የመዋደድ መንፈስ የሚያበስር ሀገራዊ ፀጋችን ነው።
የእሬቻ በዓል ዋነኛ ውበቱ የህዝቦች አብሮነት እና በህብር የተጋመደ ህብረት ነው።
በበዓሉ አከባበር ወቅት ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች የሚሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በፍቅር ተቃቅፈው፣ በህብረት ዘምረው፣ የበዓሉን የሰላም እሴቶች ከፍ ያደርጋሉ።
ይህ ህብረት ኢትዮጵያውያን ይበልጥ የሚጋመዱበት፣ ብዝሀ ውበታቸውን ከፍ አድርገው ለዓለም የሚያሳዩበት ልዩ መድረክ ነው፡፡
አብሮነት፣ መከባበር እና መተሳሰብ የሚጎለብትበት፣ ፍቅርና ሰላም የሚንፀባረቅበት እሬቻ የህዝባችንን የወንድማማችነት እና የእህትማማችነት ትስስር በማጠናከር ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታም አበርክቶው ላቅ ያለ ነው፡፡
የህዝባችን የአብሮነት እና የመተሳሰብ እሴት ጎልቶ የሚታይበት እሬቻ የይቅርታ መንፈስ የሚጎለብትበት፣ የብሩህ ተስፋ ማብሰሪያ፣ የህዝባችንን ጠንካራ መስተጋብር ማስተሳሰሪያ በመሆኑ በአብሮነት በማድመቅ ዘርፈ ብዙ እሴቶቹን ይበልጥ ማሳደግ ይገባል፡፡ – የከንቲባ ጽ/ቤት