ከ11 ዓመታት በኋላ የተከናወነው ሰፊ የኢኮኖሚ ክለሳ ኢትዮጵያን ከሳሃራ በታች ካሉ ሀገራት ሶስተኛዋ ኢኮኖሚ አድረጓታል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ከ11 ዓመታት በኋላ የተከናወነው ሰፊ የኢኮኖሚ ክለሳ ኢትዮጵያን ከሳሃራ በታች ካሉ ሀገራት ሶስተኛዋ ኢኮኖሚ አድረጓታል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ኅዳር 1/2019 ዓ.ም

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም፣ ኢትዮጵያ ላለፉት 11 ዓመታት የኢኮኖሚ ክለሳ ሳታደርግ መቆየቷን ተከትሎ፣ ባለፈው ዓመት በስታትስቲክስ ኤጀንሲ እና በዓለም አቀፍ ተቋማት ድጋፍ ከአንድ ዓመት በላይ የፈጀና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያሳተፈ ሰፊ የክለሳ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከሳሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሶስተኛዋ ኢኮኖሚ ባለቤት መሆን መቻሏን በማስረጃ የተደገፈ መረጃ እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል።

የሪፎርም ሥራዎች ኢኮኖሚውን በሚያስገርም ሁኔታ አቅም ያለው እንዲሆን ያደረጉ ሲሆን፣ አዲሱ የክለሳ ሥራ ቀደም ሲል በጂዲፒ አለካክ ሥርዓት በበቂ ሁኔታ ያልተካተቱ ዘርፎችንና ውጤቶችን ማካተት አስፈላጊ እንዳደረገው ጠቅሰዋል፡፡

ቀደም ሲል የማይታወቀው ዲጂታል ኢኮኖሚና ሞባይል ባንኪንግ ዛሬ በትሪሊየን የሚቆጠር ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ደረጃ መድረሱንም ተናግረዋል።

እንዲሁም የከተማ ኮሪደር ልማትና የሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽኦ በአዲስ መልክ መለካት መጀመሩንም አንስተዋል።

በክላስተር የሚመራው የግብርና አሠራር፣ የሌማት ትሩፋት እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራ ፍራፍሬና ቡና እምርታ ሰፊ ውጤት ቢያመጡም የቆጠራና የአለካክ ሥርዓት ማሻሻያን መጠየቃቸውንም አመላክተዋል።

በዘንድሮው ዓመት ብቻ የግብርና ዘርፍ 7.7 በመቶ ዕድገት እንደሚያመጣ ይጠበቃል ሲሉም አክለዋል።

የመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ቁጥር 3 ከነበረበት አሁን በመንግሥትና በግል ከ15 በላይ ትላልቅ ፓርኮች መድረሱንም ገልጸዋል።

በኢነርጂ በኩል የአሰላና አይሻ የንፋስ ኃይል፣ የገናሌ ዳዋና የህዳሴ ግድቦች እንዲሁም የገጠር ኦፍ-ግሪድ ሶላር ፕሮጀክቶች መካተታቸውን ተናግረዋል።

በቱሪዝምም በአንድ ቀን ሁለት ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ አቅም የተፈጠረ ሲሆን፣ በአንድ የጤና ኮንፈረንስ ብቻ ከ35 ሺህ ያላነሱ ተሳታፊዎች በአዲስ አበባ መታደማቸው ገልጸዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review