AMN – ጥቅምት 4/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የዘመናት የዲፕሎማሲ ባለቤት እንደ መሆኗ መጠን፣ ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት ተሰሚነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
ሀገሪቱ ከጥንት ጀምሮ ለሉዓላዊነቷ መከበር፣ ለፓን አፍሪካኒዝም መርሆዎች እውን መሆን እና ለአህጉራዊ አንድነት የሰራችው ሥራ ለዛሬው ከፍታዋ ጠንካራ መሠረት ሆኗታል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምስረታ ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የብዙ ወገን ዲፕሎማሲ መርህን መሬት አስይዛለች።

በተለይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንድትሆን መመረጧ የሀገሪቱን ታሪካዊና አህጉራዊ ተቀባይነት በግልጽ ያሳያል።
ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ባላት ምቹ የጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና ባላት የሕዝብ ብዛት ምክንያት በቀጣናዉ የሰላምና የጸጥታ መልህቅ ሆና ዘልቃለች።
ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስከ አፍሪካ ህብረት ባሉት መድረኮች የሰላም ማስከበር ስምሪቶች ላይ ሰራዊቷን በመላክና የቀጣናውን ውጥረት በማርገብ ረገድ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ዓለም ያመነበት ነው።

በቅርብ ዓመታት ደግሞ የዲፕሎማሲ ጉዞዋ አዲስ የኢኮኖሚና የጂኦፖለቲካዊ ቁመናን የተላበሰ ሲሆን፣ ሀገሪቱ የብሪክስ አባል ሃገራትን በይፋ መቀላቀሏ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ደረጃ እንዲሸጋገር አድርጎታል።
ይህ ትልቅ ስኬት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር ያላትን የባለ ብዙ ወገን ትብብር እና የጋራ ተጠቃሚነት መርህን በተግባር ያረጋገጠበት ሆኗል።
በአህጉራዊ የልማትና የአካባቢ ጥበቃ መስክም ኢትዮጵያ የፊት ተሰላፊነቷን አስመስክራለች።

የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል የጀመረችዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ጎረቤቶቿን ጭምር ያካተተና ለአፍሪካ አርአያ የሆነ ታላቅ ሀገራዊ ስኬት ነው።
እንዲሁም ሀገሪቱ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና በተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም ላይ የምትከተለው ፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ፣ የጋራ እድገትን የሚያስቀድም የዲፕሎማሲ ጥንካሬ ማሳያ ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ የሀገሪቱን ህዝቦች ጽናትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የማስከበር ብቃት ለዓለም ያሳየ ነው።
ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ዲፕሎማሲ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወጥቶ አጀንዳ ወደ መስጠት ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በአሁኑ ወቀት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎቿ ውስጥ ማዕከል የሆነው የባህር በር ጥያቄ ሲሆን፤ ይህም በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተ ነዉ።
እንዲህ አይነቱ አካሄድ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ህልውናና የረጅም ጊዜ የደህንነት ዋስትና የሚያረጋግጥ ብልህ የዲፕሎማሲ እርምጃ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ፣ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ከፍታ የታሪኳ፣ የጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥ፣ የሰላም አስከባሪነትና የዘመናዊ ኢኮኖሚ ዲፕሎማሲዋ ዉጤት ነው።
ሀገሪቱ አሁንም በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካ ድምፅ ሆና በመቀጠል፣ የህዝቦቿንና የአህጉሪቱን ጥቅሞች የሚያስከብር የነቃና ተጽዕኖ ፈጣሪ የዲፕሎማሲ ጉዞዋን በቁርጠኝነት አጠናክራ ቀጥላለች።
በወርቅነህ አቢዮ