መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ናቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ ናቸው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ኅዳር 17/2019 ዓ.ም

7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እያካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኑሮ ውድነትንና የገበያ ማረጋጋትን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም፣ መንግሥት የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠርና የገበያ ትስስርን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አክለውም መንግሥት የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ፣ እንዲሁም የምርት አቅርቦትንና የሥራ ዕድልን ለማስፋት በርካታ ቁልፍ ተግባራትን ማከናወኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም መሠረት አርሶ አደሩንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ ከ2 ሺህ 400 በላይ የእሁድ ገበያዎች በመላው ኢትዮጵያ መከፈታቸውን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ገበያዎች በከተሞች አካባቢ የሚስተዋለውን የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስ የራሳቸውን አዎንታዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ማዕድ የማጋራት ልምድ እየዳበረ መምጣቱ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈ መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተመሳሳይ የትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር አነስተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ለማስተማር የሚገጥማቸውን ኢኮኖሚያዊ ጫና በማቃለል የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በየክልሉ ገበያ ሳያገኙ የሚባክኑ ሰፋፊ የግብርና ምርቶች መኖራቸውን በማንሳትም፣ ምርት ካለበት አካባቢ ወደ ፈላጊ ገበያ ለማድረስ የመሠረተ ልማት ውስንነት ትልቅ ማነቆ መሆኑንና ይህንን ለመቅረፍ ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በቀጣይ ዓመታት በቂ ምግብ በማምረት የዋጋ ማረጋጋት ሥራውን ማጠናከር፣ የኃይል አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ማሳደግ፣ እንዲሁም የባቡር፣ የፈጣን መንገዶች እና ሌሎች የሚገነቡ መንገዶችን በማቀናጀት የሎጂስቲክስ ሥርዓቱን ማሳለጥ ትኩረት እንደሚሰጠው አብራርተዋል።

ይህም በአምራቹና በገበያው መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ኢኮኖሚውን በተግባር ለማንቀሳቀስ ቁልፍ ሚና እንደሚኖረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review