AMN- ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም
የከተማዋ የልማት ስትራቴጂ የነዋሪዎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረገ ሰው ተኮር አቅጣጫን በመከተል ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልፀዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት አራት ዓመታት ተኩል ውስጥ ብቻ ከሁለት ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል ብለዋል።
ይህ የሥራ ዕድል ፈጠራ ስኬት ከተማዋ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከያዘችው ሰፊ ዕቅድ አንጻር ትልቅ ምዕራፍ ሲሆን፣ ወጣቶች በኢኮኖሚው ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑና የራሳቸውን የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ምቹ ሁኔታዎች መመቻቸታቸውን ጠቅሰዋል።
በከተማዋ እየተተገበሩ ካሉ አዳዲስ የልማት እሳቤዎች መካከል የጨቅላ ህጻናት ሁለንተናዊ እድገትን ታሳቢ ያደረገው የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም ዋነኛው ነው።
እንደ ከንቲባዋ ማብራሪያ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች በሚኖሩባቸው መንደሮች ውስጥ 1 ሺህ 100 የህጻናት ማቆያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል ብለዋል።
እነዚህ ማዕከላት ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብና ወተት በማቅረብ ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወቱ ሲሆን፣ ቀደም ሲል በትምህርት ቤቶችና በአረጋዊያን ዘንድ ይተገበር የነበረውን የምገባ ፕሮግራም ወደ ጨቅላ ህጻናት ጭምር በማስፋፋት አዲስ የልማት ባህል መዘርጋቱን ከንቲባዋ አብራርተዋል።

ለፕሮጀክቱ ስኬታማነትም ከ5 ሺህ 100 በላይ ወጣቶች በጤና ኤክስቴንሽን ዘርፍ ሰልጥነው ቤት ለቤት በመንቀሳቀስ የህጻናትን እድገት የመከታተልና ለቤተሰቦች ሙያዊ የምክር አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።
ይህ ተግባር በድህነትና በልዩ ልዩ ማህበራዊ ችግሮች ምክንያት ህጻናት ሊያጡ የሚችሉትን የተሟላ እድገት ለመታደግና ጤናማ ትውልድ ለመገንባት ያለመ ሲሆን በአጠቃላይ 30 ሺህ የሚሆኑ ቤተሰቦች በልጆቻቸው አማካኝነት የምግብ፣ የጤና፣ የትምህርትና የአልባሳት ድጋፍ የሚያገኙበት የተቀናጀ ፓኬጅ ተቀርጾ እየተተገበረ ይገኛልም ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ አክለውም የከተማዋ ልማት ቁሳዊ ግንባታዎችን ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ስብዕና መገንባት ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል።
የአብርሆት ቤተ-መጽሐፍትን ጨምሮ በየክፍለ ከተማው የተገነቡ ዘመናዊ የንባብ ማዕከላትና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ወጣቶች እውቀታቸውንና አካላዊ ብቃታቸውን እንዲያሳድጉ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑ ተገልጿል።
ማንንም ወደ ኋላ የማይተውና ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በአካታችነት የሚያሳትፈው ይህ የልማት ጉዞ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባዋ አረጋግጠዋል።
በሚካኤል ህሩይ