ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛነቷን ዳግም ያረጋገጠ አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝት ይፋ ሆነ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛነቷን ዳግም ያረጋገጠ አዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝት ይፋ ሆነ
  • Post category:ታሪክ

AMN ሚያዝያ 5/2018

በኢትዮጵያ አፋር ስምጥ ሸለቆ በመካከለኛው አዋሽ የምርምር ፕሮጀክት ከ100 ሺህ ዓመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ የጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንስ (Homo sapiens) ቅሪተ አካላት እና የድንጋይ መሣሪያዎች መገኘታቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የመካከለኛው አዋሽ የአርኪዮሎጂ ጥናት ቡድን ያገኛቸውን አዳዲስና ትኩረት የሚስቡ ግኝቶች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው የአሜሪካ የሳይንስ ጆርናል “ፕሮሲዲንግስ ኦፍ ዘ ናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ” (PNAS) ላይ ታትሞ ዛሬ መውጣቱ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የአጥኚ ቡድን የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ጉዞንና ጥንታዊ የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ አዳዲስ የአርኪዮሎጂ ግኝቶችን ይፋ አድርጓል።

ጥናቱ በዶ/ር ዮናስ በየነ የተመራና ከ24 አገራት የተውጣጡ ሳይንቲስቶች የተሳተፉበት የብዙ ዓመታት ምርምር ውጤት መሆኑ ተገልጿል።

በጥናቱ የተገኘው መረጃ ኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ ሲሆን፤ በአፍሪካ የሰው ዘር አመጣጥ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተት የነበረበትን ከ900,000 እስከ 200,000 ዓመታት ያለውን ጊዜ የሚዘክሩ አዳዲስ መረጃዎችን ይዟል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለሳይንሳዊ ምርምር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ በርካታ የምርምር ሥራዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ።

በየጊዜው እየተደረጉ በሚገኙ ምርምሮችም የተለያዩ የጥንት ግኝቶች ለዓለም እየተበረከቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዛሬ ይፋ የተደረገው የምርምር ውጤት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

በምርምሩ የሆሞ ሳፒየንስ (Homo sapiens) የሰው ዘር አመጣጥን፣ ሰዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ የድንጋይ መሣሪያዎችን፣ የሰው ዘር ቅሪተ አካላትንና የተለያዩ የእንስሳት ቅሪቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ አዲስ ሳይንሳዊ የአርኪዮሎጂ ግኝቶች ኢትዮጵያ አሁንም የሰው ልጅ ዘር መገኛ መሆኗን ዳግም ለዓለም ያረጋገጡ ክስተቶች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ተመራማሪው ዶክተር ዮናስ በየነ በበኩላቸው፤ በአፋር ስምጥ ሸለቆ ሀሊቢ በተባለ ስፍራ የተገኙ ወሳኝ የአርኪኦሎጂ እና የፓሊዮአንትሮፖሎጂ ግኝቶችን የሚተነትን ሳይንሳዊ ጽሑፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ባለው “ፕሮሲዲንግስ ኦፍ ዘ ናሽናል አካዳሚ ኦፍ ሳይንስ” (PNAS) መጽሔት ላይ ዛሬ ታትሞ መውጣቱን ገልጸዋል።

በሀሊቢ አካባቢ የተደረገው ይህ ጥናት ከ100 ሺህ ዓመታት በፊት የነበረውን የሰው ልጅ አኗኗርና አካባቢያዊ ሁኔታ የሚፈትሹ አዳዲስ መረጃዎችን ይፋ ማድረጉን ጨምረው አስታውቀዋል።

በጥንቃቄ የተሰሩና ለተለያዩ አገልግሎቶች ይውሉ የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የድንጋይ መሣሪያ ስብስቦች መገኘታቸውን ጠቁመው፤ የሰው ልጅ የቴክኖሎጂ እድገት በወቅቱ ምን ይመስል እንደነበር ትልቅ ማሳያ መሆኑንም ተመራማሪው አብራርተዋል።

በወቅቱ አካባቢው የዛሬውን በረሃማ ገጽታ ሳይሆን ለምለምና ጫካማ እንደነበር የሚያሳዩ የጉሬዛ፣ የዝንጀሮ፣ ቀንድ ያላቸው እንስሳት፣ የአይጦች እና የአእዋፍ ቅሪቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

ይህም በጥንታዊው የአዋሽ ወንዝ አካባቢ የነበረውን የተመቻቸ የተፈጥሮ ሁኔታና የሰው ልጆች እንቅስቃሴ ያሳያል ብለዋል።

ሌላው የጥናት ቡድኑ አባል ተመራማሪ ዶክተር ብርሃነ በበኩላቸው፤ ጥናቱ በዋናነት ከዛሬ 100 ሺህ ዓመታት በፊት በአካባቢው ይኖሩ ስለነበሩ የመጀመሪያዎቹ ዘመናዊ የሰው ዘር ዝርያዎች (Homo sapiens) አዲስና የተሟላ መረጃ መስጠቱን አብራርተዋል።

እነዚህ አዳዲስ ግኝቶች በኢትዮጵያ የሚከናወኑ የአርኪዮሎጂ ምርምሮች በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚያሳዩ ከመሆናቸውም በላይ፣ ለሀገሪቷ የቱሪዝም ዘርፍና ለታሪክ ጥናት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ባለሥልጣኑ በቀጣይም ዝርዝር ሳይንሳዊ ትንታኔዎችን በማድረግ ግኝቶቹን በዓለም አቀፍ የሳይንስ መድረኮች ላይ ማስተዋወቁን እንደሚቀጥል ታውቋል።

ግኝቱ ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን በተጨባጭ ከማረጋገጡም በላይ፣ ጥንታዊ ሆሞ ሳፒየንሶች በአፋር ስምጥ ሸለቆ የነበራቸውን የኑሮ ሁኔታ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአካባቢ ተጽዕኖ በዝርዝር የሚያሳይ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review