AMN ሚያዚያ 7/2018
በኢትዮጵያ እየተተገበረ የሚገኘው የኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገር በቀል እውቀት የተቃኘ እና በራስ ባለቤትነት የሚመራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2026 የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) እና የዓለም ባንክ የፀደይ ወቅት ስብሰባ በዋሺንግተን ዲሲ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ከስብሰባው ጎን ለጎን በተዘጋጀ የልማት አቅም ግንባታ መድረክ ላይ ተሳትፈዋል።
እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ አጀንዳ ለከፍተኛ የዓለም አቀፍ ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች አብራርተዋል።
በስብሰባው ላይ ላይ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ፣ ከዓለም ባንክ እና ከአውሮፓ ኮሚሽን የተወከሉ ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
የባንኩ ገዥ “ገበያዎችን፣ ተቋማትን እና መረጋጋትን በፈታኝ ወቅቶች ውስጥ መገንባት” በሚል መሪ ርዕስ በሰጡት ገለጻ፤ በኢትዮጵያ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አማካኝነት በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ እየተከናወነ ያለውን መዋቅራዊ ሽግግር በዝርዝር አቅርበዋል።
በዚህም ዘርፉን ለማዘመን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን ለተሳታፊዎች አስረድተዋል።
የባንኩ ገዥ ኢትዮጵያ ወደ ወለድ ተመን ተኮር የገንዘብ ፖሊሲ ማዕቀፍ እያደረገች ያለውን ሽግግር እና በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሬ ተመን ሥርዓት ትግበራን በዋናነት አንስተዋል።

በተጨማሪም በአዲሱ የብሔራዊ ባንክ አዋጅ እና በዘመናዊ የባንክ ሥራ ሕግጋት የታገዘው የቁጥጥር ማዕቀፍ፣ የሀገሪቱን የፋይናንስ መዋቅር ሙሉ በሙሉ እየለወጠው እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የገዢው መልዕክት ዋነኛ ማጠንጠኛም የሪፎርም ባለቤትነት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሀገር በቀል እውቀት የተቃኙ እና በስትራቴጂያዊ ቅደም ተከተል የሚመሩ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ከተለያዩ አካላት የሚገኘው ማንኛውም የቴክኒክ ድጋፍም ቢሆን በሀገሪቱ ፍላጎት ላይ የተመሠረተና ከልማት የቅድሚያ ትኩረቶች ጋር የተጣጣመ እንጂ ከውጭ ተጽዕኖ የሚመነጭ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
ወደፊት ስለሚከናወኑ ተግባራት ማብራሪያ የሰጡት የባንክ ገዥው፤ በቀጣዩ ምዕራፍ የሀገር ውስጥ የፋይናንስ ገበያን ይበልጥ ማሳደግ እና ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ የሪፎርሙ ቀዳሚ አጀንዳዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
ለዚህም ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ተከታታይነት ያለው የተቋማት አቅም ግንባታ፣ የፖሊሲ ቀጣይነት እና የግል ዘርፉን የሚመራውን ኢኮኖሚ መሸከም የሚችል ጠንካራ የፋይናንስ ሥርዓት መገንባት ወሳኝ መሆኑን መግለጻቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር ለኤኤምኤን በላከው መረጃ አመልክቷል።