የዜግነት አሻራ

You are currently viewing የዜግነት አሻራ

የምርጫ ካርድ ያልወሰደ ዜጋ ሌሎች በመረጡት ፓርቲ የመተዳደርና የመመራት ግዴታ እንዳለበት ተጠቁሟል

በአዲስ አበባ ከተማ ሳሪስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪው አቶ ዳንኤል ሰለሞን በሀገራችን በተካሄዱ ባለፉት ስድስት ምርጫዎች ድምፅ በመስጠት መሳተፋቸውን ይናገራሉ፡፡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ‘ይበጀኛል’ ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምጻቸውን ለመስጠት የምርጫ ካርድ በማውጣት የድምፅ መስጫውን ዕለት እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

“በምርጫ መሳተፍ የዜግነት መብታችን ነው፡፡ መብቴን መጠቀም የመንፈስ እርካታ ይፈጥርልኛል። የሚያስተዳድሩንን ሰዎች መለወጥ ወይም እንዲቀጥሉ ማድረግ የምንችለው በምርጫ ነው፡፡ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብታችንን ለመጠቀም የምርጫ ካርድ መያዝ ይገባናል” የሚሉት አቶ ዳንኤል፣ ከቤተሰባቸው ውስጥ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ ሆኖት የምርጫ ካርድ ያልወሰደ የለም፡፡ ጓደኞቻቸውም በምርጫው እንዲሳተፉ መረጃ እንዳደረሷቸው ተናግረዋል፡፡ በምርጫው “እኔን ይወክለኛል” የሚሉት አካል ባይመረጥ እንኳን መብታቸውን በመጠቀማቸው እንደማይጸጸቱ እና ውጤቱን በጸጋ እንደሚቀበሉ አብራርተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ጀሞ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ ማሞ ገበየሁም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ ለማድረግ የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡ “በሀገራችን የምንፈልገውን ዘላቂ ሰላምና ልማት በአመፅና በግጭት ማምጣት አይቻልም። ይህን ማሳካት የምንችለው በሰላማዊ መንገድ፤ በምርጫና በምርጫ ብቻ ነው” ይላሉ፡፡

አቶ ማሞ ለራሳቸውና ለሀገር የሚበጅ ሐሳብ ያለው የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ እንደሆነ ለመለየት በቴሌቪዥን የሚካሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የክርክርና ቅስቀሳ መድረኮችን እየተከታተሉ ነው፡፡ “ምርጫ የምንፈልገውን ለማምጣት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ ምርጫውን አለመጠቀም ኪሳራ፤ የዜግነት መብትንም አለመጠቀም በመሆኑ ሁሉም ዕድሉን መጠቀም አለበት” ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ወይዘሮ ፍቅርተ ግርማ በአዲስ አበባ ሽሮሜዳ አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በኢትዮጵያ በተካሄዱ ምርጫዎች ድምፅ በመስጠት ተሳትፎ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ምርጫው ‘ሕይወቴን ያሻሽልልኛል፤ ለሀገር የሚጠቅም ነገር ይሠራል’ ተብሎ እምነት የሚጣልበት የፖለቲካ ፓርቲ የሕዝብ ድምፅ አግኝቶ ወደ ኃላፊነት የሚመጣበትን ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ፤ ይህንን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ያነሳሉ፡፡ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ከምንም በላይ ‘በሀገራችን ሰላምና መረጋጋት እንዲሁም ልማት ያመጣል’ ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት የምርጫ ካርድ ማውጣታቸውን ይናገራሉ፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ደሳለኝ ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ ምርጫ ዜጎች ይሁንታቸውን የሚያሳዩበት፣ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያዊ ዜግነታቸው የሚያገኙት የመምረጥና መመረጥ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 38 መሠረት “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለካከት ወይም አቋም ላይ የተመሠረተ ልዩነት ሳይደረግበት በማናቸውም የመንግሥት ደረጃ በየጊዜው በሚካሄድ ምርጫ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት አለው። ዕድሜው 18 ዓመት እና ከዚህ በላይ የሆነ ሰው የመምረጥ መብት አለው።”

ምርጫ ዜጎች ለቀጣይ አምስት ዓመት እንዲመራ ለሚፈልጉት አካል በነጻነት ድምፃቸውን በመስጠት ውክልና የሚሰጡበት ሂደት ነው። ምርጫ ወቅታዊ፣ በጊዜ የተገደበና ሕገ መንግሥታዊ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ እንደሚገልጹት፣ ምርጫ ዜጎች በነጻ ፈቃዳቸው መንግሥትን መምረጥ እንደሚችሉ፣ አብላጫ ድምፅ ያገኘው የፖለቲካ ፓርቲ ከሕዝብ በሚመነጭ ይሁንታ ወይም ዜጎች በሚሰጡት ድምፅ ተመርጦ ሀገርን መምራት እንደሚችል የሚረጋገጥበት ሂደት ነው፡፡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ልምምድ መሠረት የሚጣልበትና በሂደት እየተጠናከረ የሚሄድበትን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሥልጣን የሕዝብ መሆኑን፣ ሕዝብ በምርጫ ካርድ ሥልጣን እንደሚሰጥና ከዚህ ውጭ በማንኛውም ሁኔታ መያዝ እንደማይቻል ያስተምራል፡፡

ዜጎች የሚተዳደሩት በሕገ መንግሥትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ መሠረት እንደመሆኑ፣ ምርጫ ይህን ሕግ የማክበርና የማስከበር፣ በዚያም የመመራት ልምምድ ያስገኛል፡፡ ለሀገር ሉዓላዊነት፣ ለዜጎች መብትና ነጻነት፣ ለፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ ለዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት መጠናከርም ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ፣ ዜጎች በምርጫ የመሳተፍ የሕግ ግዴታ ባይኖርባቸውም የሞራል ወይም የውዴታ ግዴታ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ለነገዋ ኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታና ለተሻለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ ሂደት ነውና፡፡

የምርጫ ካርድ በማውጣት ድምፅ መስጠት ዜጋዊ፣ ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፋዊ መብት ነው፡፡ የዜግነት መብት ነው ሲባል ኢትዮጵያዊ የሆነና የፍርድ ቤት ክልከላ እስካልተጣለበት ድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት የተጎናጸፈው መብት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ዕውቅና የተሰጠው ነው፡፡ ይህንን በሕይወታችን ላይ ለውጥ የሚያመጣ ወርቃማ ዕድል አለመጠቀም የዜግነት መብትን አለመጠቀም ወይም የመብት መጓደል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል የሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ የምርጫ ህግ መሰረት በድምፅ መስጫው ዕለት እድሜ 18 እና ከዚያ በላይ የሆነው በመራጭነት መመዝገብ ይችላል። በአዕምሮ ሕመም ምክንያት የመወሰን አቅም የሌለው መሆኑ ሥልጣን ባለው አካል ወይም በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠበት እና በፍርድ ቤት በመምረጥ እንዳይሳተፍ ክልከላ የተጣለበት በመራጭነት መሳተፍ አይችልም፡፡

የምርጫ ካርድ ያልወሰደ ዜጋ ሌሎች በመረጡት ፓርቲ የመተዳደርና የመመራት ግዴታ አለበት፡፡ “አንተ መምረጥ ሲገባህ ያልመረጥከውን ነገር በሙሉ ሌሎች ሰዎች ይመርጡልሃል” እንደሚባለው በምርጫ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ሕጋዊ አካሄድ፣ የዴሞክራሲ አንዱ መገለጫና ከዜጎች የሚጠበቅ ኃላፊነት እንደሆነ የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ አስረድተዋል፡፡

ዜጎች መብታቸውን

እንዲጠቀሙ  ምን እየተሠራ ነው?

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ 1133/2013፣ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ 1162/2011 መሠረት በምርጫ ዙሪያ ትምህርትና ግንዛቤ የመስጠት ኃላፊነት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ቦርዱ መራጮች በቂ ምርጫ ነክ ግንዛቤ የሚያገኙበትን ስልት በመቀየስና የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የመራጮች ትምህርት ይሰጣል፡፡ የመራጮች ትምህርት መስጠት እንዲችሉ ሕጋዊ ሰውነት ላላቸው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማት የማስተማር ፈቃድ እንደሚሰጥ የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ ያነሳሉ፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱ ሥር የሰደደ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችና መንግሥትም ኅብረተሰቡ በነቂስ ወጥቶ ምርጫ ካርድ እንዲወስድ በመቀስቀስና በማሳመን መሳተፍ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ካልታከለበት ምርጫ እውነተኛ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ ሊሆን አይችልም፡፡

ምርጫ “አያገባኝም፤ ማንም ሊያስተዳድረኝ ይችላል” በሚል በቸልተኝነት የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። ከዚህ አኳያ ዜጎች ካርድ በመውሰድ፣ የተሻለ ሕይወታቸውን የሚለውጥ፣ ሀገርን ወደ ዕድገትና ብልፅግና የሚወስድ ፖሊሲና ፕሮግራም ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥና ድምፅ መስጠት እንደሚገባቸው የሕግ ባለሙያው አቶ ጥጋቡ አስረድተዋል፡፡

አቶ አህመድ ሁሴን የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር ዕውቅና የተሰጣቸው 5 ሺህ 700 የሚሆኑ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶችን በአባልነት አቅፎ ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት መሠረት ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድና ሀገርን የሚመራ መንግሥት የሚመጣበት ሂደት ነው፡፡ የሁሉም ዜጋ ድምፅ የሚሰማበት፣ እኩልነታቸው የሚረጋገጥበት፣ የመምረጥና የመመረጥ መብታቸውን የሚጠቀሙበት ሂደት ነው፡፡ ምርጫ ካርድ በመውሰድ የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ መምረጥ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ አይደለም፡፡ የአንድ ሀገር ሕልውና እና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት ነው፡፡ ዜጎች የሰጡትን ዕድል መጠቀም ያልቻለ የፖለቲካ ፓርቲን በካርዳቸው ሊነጥቁ እንደሚችሉ የሚተማመኑበት ሂደት ነው። በምርጫ ተሳትፎ አለማድረግ ዕድልን ማባካን፣ መብትን አለመጠቀም፣ ትልቅ ሀገራዊ ኹነት ላይ አለመሳተፍ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡

እንደ ምክር ቤትም ኅብረተሰቡ የምርጫ አስፈላጊነትን በመረዳት በምርጫው ሂደት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ አጀንዳ በማድረግ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከ200 በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማኅበራት ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዕውቅና በማግኘት መራጮች የምርጫ ጠቀሜታና አስፈላጊነት ተገንዝበው፣ በፍላጎትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በመራጮች ትምህርትና በታዛቢነት ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ ማኅበራቱ ማኅበረሰቡን በገጽ ለገጽ፣ ለመምህራንና በየቀበሌው ላሉ ተወካዮች የአሰልጣኞች ሥልጠና በመስጠት፣ ሰዎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸው እንደ ገበያ ባሉ አካባቢዎች በሞንታርቦ አዝናኝ በሆነ መንገድ መልዕክቶችን በማዘጋጀት ለምርጫው ትኩረት እንዲሰጡ ቅስቀሳዎች በማድረግ ተደራሽ ለመሆን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የሚከራከሩበት መድረክ እንዲመቻች በማድረግ ኅብረተሰቡ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት ለምሳሌ እሳቸው በዳይሬክተርነት የሚመሩት “ፕሮ ዲቨሎፕመንት ኔትዎርክ” የተሰኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ጭምር ሶማሌ፣ ድሬዳዋ፣ አፋርና ሐረር ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር እንዲያደርጉ መድረክ በማመቻቸትና በክልል ቴሌቪዥን እንዲተላለፉ በማድረግ ሕዝቡን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዘንድሮው ምርጫም በተመሳሳይ መድረኮችን በማመቻቸት፣ ኅብረተሰቡ ሊገባው በሚችለው ቋንቋ የምርጫ ግንዛቤው እንዲያድግ ማድረግ ላይ እንደሚሠሩ አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የሲቪክ ማኅበራት በሰላም ዙሪያ ግንዛቤ በመፍጠር ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድና በየክልሉ ካሉ የፀጥታ አካላት ጋር በመገናኘት የኅብረተሰቡ ደህንነት እንዲጠበቅ የበኩላቸውን ሚና ለመወጣት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ “በምርጫ መሳተፍ መብት ብቻ ሳይሆን ኃላፊነትም ጭምር ነው” የሚሉት አቶ አህመድ ምርጫው ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው። መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምርጫው ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ በማስተካከል ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያ በተለያዩ አካባቢዎች ሰላም እንዲፈጠር ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለምርጫ ሕብረት (CECOE) ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ኃይለማርያም ከአንድ ወር በፊት ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፣ ሕብረቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም የመራጮች ትምህርት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለዚህም አባል ድርጅቶች የመራጮች ትምህርትን እንዲያካሂዱ የሚያስችላቸውን የበጀት ድጋፍ አግኝተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡ “የእሷ ድምፅ” በሚል የሬዲዮ ፕሮግራም የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የግንዛቤ ፈጠራ ሥራዎች እያከናወኑ ናቸው፡፡ ሕብረቱ በይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽና በመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ እየፈጠረ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ዜጎች የመምረጥና መመረጥ መብታቸውን እንዲጠቀሙና የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡ መደበኛ መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ለምሳሌ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፌዴራሊዝምን ጨምሮ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ክርክር እንዲያደርጉ መድረክ በማመቻቸት በመገናኛ ብዙኃን እንዲሰራጭ ተደርጓል፡፡ ከ432 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የቦርዱ ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ዜጎች በነጋቸው ጉዳይ ለመወሰን የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ እንዲያወጡ አጫጭር የቪዲዮ መልዕክቶች በመልቀቅ እያሰራጨ ይገኛል፡፡ ወደ አንድ ሺህ የሚሆኑ በየክልሉ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከማኅበረሰቡ የተውጣጡ በጎ ፈቃደኞችን በማሰልጠን በሚኖሩበት አካባቢ ለሚገኝ ማኅበረሰብ የመራጮች ትምህርት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል። በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት ለመስጠት በርካታ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕውቅና በመስጠት እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review