በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም መሰል መሰናዶዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ መካከል መጽሐፍ፣ የሥነ ጥበብ አውደ ርዕይ እና ቴአትር ይገኙበታል። ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
“አመጋገብ ለተሻለ ብቃት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው የስፖርት ሥነ- ምግብ መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሥነ- ምግብ ባለሙያ በሆነው ዳንኤል ክብረት (ዶ/ር) ነው፡፡ መጽሐፉ ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች፣ ዳኞች እና የመገናኛ ብዙሀን አባላት በተገኙበት ተመርቆ ለንባብ በቅቷል፡፡
በሌላ መረጃ “ክቡር ልጆች” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ በነገው እለት ውይይት ይደረጋል፡፡፡ በብርሃኑ በላቸው በተጻፈው እና በታዋቂው የልጆች መጽሐፍ ላይ ውይይት የሚካሄደው ከሣር ቤት ወደ ቫቲካን ኤምባሲ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው የኢትዮጵያ ሥነ መለኮት ድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲሆን መርሃ ግብሩ የሚጀመረው በ9፡00 ሰዓት ነው፡፡
በተጨማሪም በዛሬው እለት የመጽሐፍ ፊርማ ሥነ ስርዓት ይከናወናል፡፡ በጃዕፈር መጽሐፍት መደብር በሚካሄደው በዚህ መርሃ ግብር ደራሲ ሃይሉ አርአያ የመጽሐፍ ፊርማ፣ ከአንባቢያን ጋር የመወያየትና ፎቶ የመነሳት መርሀግብር ያካሂዳል፡፡ መርሃ ግብሩ ከቀኑ 8፡00 እስከ 10፡00 ሰዓት ለገሃር በአዲሱ የጃዕፈር መጽሐፍት መደብር ይካሄዳል፡፡
የሥነ-ጥበብ አውደ ርዕይ
“በሰማይ እና በምድር መካከል” የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ሊጠናቀቅ ቀናት ቀሩት፡፡ የሰዓሊ መላኩ አየለ ስራዎች የቀረቡበት ይህ አውደ ርዕይ ሚያዝያ 19 ቀን 2018 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡ አውደ ርዕዩ የሚታየው ሀያት ሪጀንሲ ሆቴል በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ሲሆን መግቢያው በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስትያን በኩል ነው፡፡
በሌላ መረጃ የእዮብ ኪታባ የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ “ከጣራ በታች” የተሰኘው ይህ የስዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ የሚገኘው በገብረክርስቶስ ደስታ ሞደርን አርት ሙዚየም ውስጥ ሲሆን እስከ ሚያዝያ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በእይታ ላይ ይቆያል፡፡
የቴአትር መርሃ-ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። ቅዳሜ ከ7፡30 ሰዓት “12ቱ እንግዶች” እንዲሁም 11፡30 ሰዓት “ሸምጋይ”፣ እሁድ በ7፡30 ሰዓት “ንጉሥ አርማህ” እንዲሁም በ11፡30 ሰዓት “እምዩ ብረቷ” ቴአትሮች በብሔራዊ ቴአትር ይታያሉ። ተመልካቾች ጊዜያቸውን ለመቆጠብ በ“ሁሉ በጄ” መተግበሪያ በመጠቀም ትኬቶችን አስቀድመው መግዛት እንደሚችሉ ተገልጿል። እንዲሁም “የመጨረሻው ፍርድ” ቴአትር እሁድ በ11:30 ሰዓት በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ይታያል፡፡
በጊዜው አማረ