በአፍሪካ ፈር ቀዳጁን አገልግሎት አዲስ አበባ ጀምራለች

You are currently viewing በአፍሪካ ፈር ቀዳጁን አገልግሎት አዲስ አበባ ጀምራለች

AMN-ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ ዛሬ በአፍሪካ ፈርቀዳጅ የሆነውን ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ አስጀምራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጥር 26 ቀን 2018 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በሶስት ወራት ውስጥ እንደሚጀመር ተናግረው ነበር።

የመንግሥትን አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በሰጡት ማብራሪያ ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በተቋም ደረጃ ማዳረሱ በቂ ስላልሆነ ፣ ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል በአውቶቡስ ቨርቹዋል ማዕከል እየተሠራ መሆኑን ጠቁመው ነበር። ወደ ተግባር ለመግባትም ሶስት ወራት እንደሚወስድ ነበር የጠቀሱት።

ቃል በተግባር ሦስት ወራቱ ሳይደፍን ተፈጽሟል። አዲስ አበባ ፣ አውቶብስን በመጠቀም ተንቀሳቃሽ የመሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር የተሰጠውን አቅጣጫ ወደ ተግባር በማስገባት ፈርቀዳጅ ሆናለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተናገሩ በሁለት ወራት ከ19 ቀናት ተንቀሳቃሽ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ፣ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት አገልግሎቱ በይፋ ተጀምሯል።

ከዚህ ቀደም የተለያዩ አገልግሎቶቿን በመሶብ የአንድ ማዕከል ስትሰጥ የነበረችው አዲስ አበባ አሁን ላይ የአገልግሎት አሰጣጡን ከፍ ወዳለ ደረጃ በማሳደግ ቀዳሚ ሆናለች።

በተጨማሪም በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ በፊት ከሚሰጡ 17 አገልግሎቶች መካከል በዛሬ እለት በአዲስ አበባ ከተማ 8 የአዲስ መሶብ ተንቀሳቃሽ ዲጅታል የመንግስት አገልግሎቶች በይፋ ተጀምረዋል፡፡

በአዲስ መሶብ ዲጅታል የአንድ ማዕከል በተንቀሳቃሽ አውቶቡስ የሚሰጡ አገልግሎቶች የገቢ አገልግሎት (አዲስ ቲን ማውጣት)፣ የንግድ አገልግሎት (ንግድ ፈቃድ ማውጣት፣ ማደስ)፣ የጤና (ለመንጃ ፈቃድ አካላዊ የጤና ምርመራ)፣ የሲቪል ምዝገባ (የመታወቂያ ዕድሳት እና ልደት)፣የአሸከረካሪ ተሽከርካሪ (የመንጃ ፈቃድ እና የቦሎ ዕድሳት)፣የኢትዮ ፖስታ (የመንገድ ፈንድ ክፍያ)፣ የብሔራዊ መታወቂያ (አዲስ ምዝገባና የመረጃ እርማት)፣የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት (ቅድመ ክፍያ) አገልግሎቶች ናቸው ተብሏል።

አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የዘመነች ከተማነቷን በተግባር የሚያረጋግጥ ርምጃ ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

በታደሰ ሽፈራዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review