AMN- ሚያዚያ 17/2018 ዓ.ም
የነዳጅ አቅርቦት ስርጭት እና የአገልግሎት አሰጣጡን ይበልጥ ከማሻሻል ባሻገር የስርጭትና ቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፈው አንድ ወር በተካሄደ የነዳጅ ስርጭት፣ ቁጥጥርና ክትትል ዙሪያ የሥራ ሪፓርት የቀረበ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እና የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ሃቢባ ስራጅ ተሳታፊዎቹን አወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ለከተማ አስተዳድሩ የተደለደለው የናፍጣ መጠን ባለፍው አንድ ወር ውስጥ 37 ሚሊየን 687 ሺህ 500 ሊትር ሲሆን ከዚህም ውስጥ 31 ሚሊየን 682 ሺህ 855 ለመደበኛ ነዳጅ ተጠቃሚ ማህበረሰብ እንዲቀርብ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በፌደራል ደረጃ ለተለዩ እና የተፈቀደላቸው ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሩ ለተለዩ ኢንዱስትሪዎችና በከተማ አስተዳዳሩ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የተካተቱን ጨምሮ 1041 ተቋማት በድምሩ 6 ሚሊየን 4 ሺህ 645 ሊትር ናፍጣ በትስስር እንዲወስዱ ተደርጓል ።
የከተማ አስተዳድሩ የነዳጅ ስርጭት ግብረ ኃይል የነዳጅ ስርጭቱ ፍትሃዊ እና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን 24/7 ከፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛል ። በተለይም በህገወጥ የነዳጅ ዝውውር የተሳተፉ 256 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጿል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች መካከል አመራሮች፣ የጸጥታ ኃይሎች፣ የመንግስት ሰራተኞች ፣ የማደያ ሰራተኞች፤ ህገ ወጥ ሰልፍ አሰላፊ ወጣቶች፣ ደላላዎችና ሾፌሮች እንደሚገኙ ግብረ ኃይሉ አስታውቋል ።

ዉይይቱን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በቀጣይ የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት እና የአገልግሎት አሰጣጡ እንዲሻሻል በማድረግ የስርጭትና ቁጥጥር ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
በውይይቱ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የክ/ከተሞች ንግድ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በወንድምአገኝ አበበ