AMN – ግንቦት 4/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙት የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፤ በነዋሪው አስተሳሰብ፣ ጤና እና የእለት ተእለት የኑሮ ዘይቤ ላይ መሰረታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑ ተገለጸ።
የከተማ አስተዳደሩ በልዩ ትኩረት እየተገበራቸው የሚገኙት እነዚህ የልማት ሥራዎች፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ለዘመናት የቆየውን የከተማ የኑሮ ባህል ወደ አዲስ ምዕራፍ እያሸጋገሩት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት ቴክኒካል አማካሪ አቶ ዋለልኝ ዳሳለኝ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ገልፀዋል። አቶ ዋለልኝ እንደገለጹት፣ የኮሪደር ልማቱ አዲስ የአኗኗር ዘይቤን ከማስተዋወቁም በላይ ማህበራዊ መስተጋብርን በእጅጉ አጠናክሯል።

ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ መሰረተ ልማቶች መገንባታቸው ቀደም ሲል በቤት ውስጥ ተወስኖ የነበረውን የመዝናኛ ባህል ወደ አደባባይ እንዲወጣ አስችሏል፡፡
ሰፋፊ የእግር መንገዶች እና የብስክሌት መስመሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕፃናት መጫወቻ ሥፍራዎች እንዲሁም በየመንገዱ የተዘጋጁ ማረፊያ ሥፍራዎች ከግንባታዎቹ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
ይህም ማህበረሰቡ በጋራ እንዲገናኝ፣ እንዲወያይ እና ማህበራዊ ትስስሩን እንዲያጎለብት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አማካሪው ጠቁመዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በከተማዋ የተጀመሩት የምሽት ግብይቶች የከተማዋን ድባብ በማነቃቃት ለኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ተጨማሪ ጉልበት መሆናቸው ጠቅሰዋል።

እነዚህ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች በሳምንት ሰባት ቀን፣ በቀን 24 ሰዓት (24/7) በመሰራታቸው በነዋሪው ዘንድ “የማይቻል የለም” የሚል ስነ-ልቦናዊ ጥንካሬ እንዲገነባ አድርገዋል።
ይህም የዜጎችን የአስተሳሰብ ለውጥና የባለቤትነት ስሜት ከማሳደጉም በላይ፣ የአካባቢ ጽዳትና ውበትን መጠበቅ የጥቂቶች ኃላፊነት ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ግንዛቤ አስጨብጧል።
የአረንጓዴ ስፍራዎች መስፋፋትና የወንዝ ዳርቻዎች መጽዳት ነዋሪዎች ንጹሕ አየር እንዲያገኙ ከማድረጉም ባሻገር፣ ተጨማሪ ወጪ ሳያስፈልግ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ መነሳሳትን ፈጥሯል።

ይህ አዲስ ክስተት ወጣቶች ከአላስፈላጊ ሱሶች እንዲርቁና ከእንቅስቃሴ ማነስ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ አቅም መፍጠሩን አቶ ዋለልኝ አስገንዝበዋል።
በአጠቃላይ የአዲስ አበባ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ከተማዋን ለኑሮ ተመራጭ ከማድረግ ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ሁለንተናዊ ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ የላቀ ፋይዳ እያበረከተ ይገኛል።
በበረከት ጌታቸው